ነሃሴ 08/2013 (ዋልታ) – አሸባሪው ሕወሃት ሀገር ባስተዳደረባቸው ዓመታት የኪነ ጥበብ ተቋማትን በማፍረስ ኢትዮጵያዊነት እንዳይጎላ፣ መከፋፈል እንዲፈጠር ሲሰራ ቆይቷል።
ብሔራዊ የኪነ ጥበብ አስተባባሪ ኮሚቴ አባልና የኪነ ጥበብ ባለሙያ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ በየብሄረሰቡ መልከ ብዙ ባህላዊ የማጀገኛ ኪነ ጥበባት ይገኛሉ።
ኢትዮጵያዊያን በታሪካቸው ሰላምና ፍቅር ወዳድ በመሆናቸው ሌሎችን የመውረርና የማጥቃት ታሪክ እንደሌላቸው አንስተዋል።
ወረራና ጥቃት ሲፈጸምባቸው ግን በሕብረት መክተው ደማቅ ታሪክ መጻፋቸውን አውስተው፤ “ለዚህ ደግሞ በየማህበረሰቡ ያሉ ባህላዊ ከያኒያን ጠላትን ለመመከት ሃይልና ደጀን ሆነዋል” ብለዋል።
አገር ስትወረርና ሉዓላዊነቷ ሲደፈር ሙዚቃ፣ ግጥምና ሌሎች የኪነ ጥበብ ትሩፋቶች ማህበረሰቡን በማነቃቃትና ሠራዊቱን በማጀገን ትልቅ ሚና መጫወታቸውን ነው ያብራሩት።
ከሰሃራ በታች በሚገኙ አገራት በቀዳሚነት የሚነሳው የአገር ፍቅር ቴአትር ቤት መስራች ከያኒያንም የፋሺስት ኢጣሊያ ወረራን ለመመከት አርበኞችን ለማጀገን፣ የመዋረድና የመሸነፍን ክፋትና የድልን ከፍታና ጥልቀትን ለማሳየት መሰባሰባቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል።
“ሀገር ፍቅር ቴአትርን ጨምሮ በርካታ የኪነ ጥበብ ማዕከላትና አደረጃጀቶች ተቋቁመው የአገር ፍቅርና ኢትዮጵያዊ አንድነትን እንዲጎላ ትልቅ ሚና ነበራቸው” ብለዋል ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ።