የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ የመሬትና መሬት ነክ አገልግሎቶችን ላልተወሰነ ጊዜ እንዲታገዱ ውሳኔ አስተላለፈ

ነሃሴ 08/2013 (ዋልታ) -የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ከአርብ ነሐሴ 7 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ለመሬት አስተዳደር ተቋማት፣ ለመሠረተ ልማት ቅንጅት እና ግንባታ ፈቃድ ባለስልጣን እንዲሁም ለ11ዱም ክፍለ ከተሞች ባስተላለፈው ሰርኩላር ፣ የመሬት እና የመሬት ነክ አገልግሎቶች ላልተወሰነ ጊዜ ሙሉ በሙሉ እንዳይሰጡ ውሳኔ አስተላልፏል ።
ካቢኔው ዕግዱን ያስተላለፈው በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ትኩረታቸውን በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በማድረግ ሲሆን አንዳንድ ስግብግብ ግለሰቦች ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታውን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም በአቋራጭ ለመክበር በመሬትና መሬት ነክ አገልግሎቶች ላይ ትኩረት በማድረግ በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸውን የከተማ አስተዳደሩ በመገንዘቡ ነው።
በዚህም ምክንያት ማንኛውም መሬትና መሬት ነክ አገልግሎት ላልተወሰነ ጊዜ የታገደ ሲሆን በስድስቱም የመሬት ነክ ተቋማት ፣በ11ዱም ክፍለ ከተሞች እና የመሠረተ ልማት ቅንጅት እና ግንባታ ፈቃድ ባለስልጣን የመሬት አገልግሎቶችን እንዳይሰጡ ወሳኔ መተላለፉን ከአስተዳደሩ የፕሬስ ሰክሪታሪያት የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡