ቦርዱ የመራጮች ምዝገባ ያልተደረገባቸውንና የተቋረጡ ምርጫ ክልሎችን አስመልክቶ ውሳኔ አስተላለፈ

ነሀሴ 17/2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመራጮች ምዝገባ ባልተካሄደባቸው እና በተቋረጠባቸው ምርጫ ክልሎችን አስመልክቶ ውሳኔ አስተላለፈ።

በመራጮች ምዝገባ ሂደት ላይ በታዩ ጉልህ ግድፈቶች፣ በመራጮች ምዝገባ ላይ በቀረቡ አቤቱታዎችን ለማጣራት ጊዜ በማስፈለጉ እንዲሁም ከጸጥታ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች የተነሳ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ድምፅ አሰጣጥ ያልተደረገባቸው ቦታዎች እንዳሉ ይታወቃል።

በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሥራ አመራር ቦርድ ቀሪ ምርጫ ያልተከናወነባቸው የምርጫ ክልሎችን፣ የምርጫው ሂደት ያለበትን ሁኔታ እና የመሳሰሉትን በመገምገም የሚከተሉትን ውሳኔዎች አስተላልፏል።

በሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የመራጮች ምዝገባ በሚመለከት በሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በ10 የምርጫ ክልሎች ላይ የመራጮች ምዝገባን የሚመረምር ከተለያዩ ሲቪል ማኅበራት የተወጣጣ አጣሪ ቡድን በመላክ የመራጮች ምዝገባ ሂደት ላይ ቀረቡትን አቤቲታዎች አጣርቷል።

በክልሉ ምርመራ ከተደረገባቸው የምርጫ ክልሎች መካከል፦

1.የአጣሪ ቡድኑ ግኝትን መሠረት በማድረግ፣ የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ክልሎች – ጅጅጋ 1 ምርጫ ክልል እና ጅጅጋ 2 ምርጫ ክልል፤ የክልል ምክር ቤት ምርጫ ክልሎች – ቀብሪደሃር ከተማ ምርጫ ክልል፣ ቀብሪደሃር ወረዳ ምርጫ ክልል፣ መኢሶ ምርጫ ክልል እና አፍደም ምርጫ ክልል የመራጮች ምዝገባ ሙሉ ለሙሉ በድጋሚ እንዲከናወን ወስኗል።

የመራጮች ምዝገባ የሚደገምባቸው በተወሰኑ ምርጫ ጣቢያዎች

– ዋርዴር ምርጫ ክልል ውስጥ አዶ ቀበሌ – 1 ምርጫ ጣቢያ እና ኤልድብር ቀበሌ – 2 ምርጫ ጣቢያዎች

– ፊቅ ምርጫ ክልል -01 ቀበሌ ምርጫ ጣቢያ 01 – 1 ምርጫ ጣቢያ

– ገላዴን ምርጫ ክልል – 1 ምርጫ ጣቢያ

– ጎዴ ከተማ ምርጫ ክልል – 4 ምርጫ ጣቢያዎች

– ምሥራቅ ኢሜ ምርጫ ክልል- 3 ምርጫ ጣቢያዎች

– ቤራኖ ምርጫ ክልል – 3 ምርጫ ጣቢያ

  1. በቀሩት የመራጮች ምዝገባ አቤቱታ የተነሳ የመራጮች ምዝገባ ሂደቱ የመራጮች ምዝገባ ቀናት ከመጠናቀቃቸው በፊት በመቋረጡ፣ የመራጮች ምዝገባ በተቋረጠባቸው ቦታዎች ሁሉ ለ5 ቀናት ያህል የመራጮች ምዝገባ ተሟልቶ እንዲጠናቀቅ ተወስኗል።

በሐረሪ ክልላዊ መንግሥት የመራጮች ምዝገባ በሚመለከት

በሐረሪ ክልላዊ መንግሥት የመራጮች ምዝገባ ቦርዱ በሰጠው የአመዘጋገብ አሰራረር መሠረት ባለመከናወኑ ተቋርጦ ቦርዱ በሚሰጠው ውሳኔ መሠረት እንደሚከናወን መገለጹ ይታወሳል። በዚህም መሠረት ቦርዱ በሃረሪ የተከናወነውን የመራጮች ምዝገባ ከመረመረ በኋላ የሚከተለውን ውሳኔ አሳልፏል።

  1. በጀጎል ዙሪያ እና ሁንደኔ የምርጫ ክልል ምዝገባው በተለያየ የክልል እና የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች የሚመርጡትን የሐረሪ ብሔረሰብ ተወላጆችን እና ከብሔረሰቡ ውጪ ያሉ ተወላጆች ተቀላቅለው በመመዝገባቸው ምዝገባው ተለያይቶ እንደአዲስ ምዝገባ እንዲካሄድ ወስኗል።
  2. በጀጎል ልዩ ምርጫ ክልል የመራጮች ምዝገባ ተቋርጦ ስለነበር ለ5 ተጨማሪ ቀናት የማሟያ ምዝገባ እንዲከናወን ተወስኗል።
  3. በሰበር ችሎት በተወሰነው መሠረት ከክልሉ ውጪ የሚኖሩ የብሔረሰቡ ተወላጆች የሚመርጡባቸው ምርጫ ጣቢያዎች በሚከተሉት ቦታዎች የሚቋቋሙ ይሆናል።

– አዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር

– ኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል ( አዳማ፣ ጭሮ፣ ኮምቦልቻ፣ ጉርሱም፣ ፈዲስ፣ ደደር እና ሃሮማያ)

– ድሬዳዋ ከተማ መስተዳድር

– ሶማሌ ብሔራዊ ክልል

– ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ያለአግባብ ምዝገባ የተከናወነባቸው የምርጫ ክልሎች የድጋሚ ምርጫ ሙሉ ለሙሉ እንዲከናወን ወስኗል። እነሱም

– ዘልማም ምርጫ ክልል

– ዲዚ ልዩ ምርጫ ክልል

– ሱርማ ምርጫ ክልል

– ሙርሲ ምርጫ ክልል

– ማጀት መደበኛ ምርጫ ክልል (ከልዩ ምርጫ ክልሎች ውጪ ያሉት ነዋሪዎች የሚመዘገቡበት) ናቸው። በደ/ብ/ብ/ህ ክልል በጉራፈርዳ ወረዳ የሚገኙ በቴፒ እና ሸኮ ልዩ የሚጠቃለሉ ጣቢያዎችን በተመለከተ ቦርዱ ተጨማሪ ውሳኔን የሚያስተላልፍ መሆኑን  ቦርዱ አስታውቋል።