ብሔራዊ የምግብ እና ስርዓተ ምግብ የአስር አመት እስትራቴጂ ይፋ ተደረገ

ነሃሴ 20/ 2013  (ዋልታ) – ብሔራዊ የምግብ እና ስርዓተ ምግብ የአስር አመት  እስትራቴጂ ይፋ ማድረጊያ እና የሰቆጣ ምግብ ማስፋፊያ ፕሮግራም  ማስጀመሪያ መድረክ በመካሄድ ላይ ነው።

መድረኩ ከ2 አመት በታች የሆኑ ህፃናትን በ2022 ከመቀንጨር ችግር ነፃ ለማድረግ የሚረዳ የሰቆጣ ቃልኪዳን የማስፋፋት ምዕራፍ ይፋ የሚደረግበት ነው።

ለቀጣይ 10 አመታት ኢትዮጵያ የምትጠቀምበት ብሔራዊ የምግብ እና እስትራቴጂ ተግባራዊ ለማድረግ ይፋ በተደረገበት በዚህ መድረክ እስትራቴጂውን በታለመው ልክ ተግባራዊ ለማድረግ ከ111 ቢሊየን ብር   ያስፈልጋል ተብሏል።

የስርዓተ ምግብ ችግር የማህበረሰብን ምርታማነትን የሚቀነስ  ነው ያሉት የመድረኩ የክብር እንግዳ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በመቀንጨር ብቻ በየአመቱ ከሀገሪቱ ጠቅላላ ገቢ 55.5 ቢሊየን ብር እንድናጣ ያደርገናል ብለዋል።

በህዳር 2011 በሚኒስትሮች ምክር ቤት በፀደቀው የስርዓተ ምግብ ፖሊሲ ይህንን ለመቅረፍ በርካታ ስራዎች ቢከናወኑም ቀሪ ስራዎች ይጠበቁብናል ብለዋል።

አያይዘውም  አሁን ሀገሪቱ ባጋጠማት ችግር ምክንያት የስርዓተ ምግብ ችግር ሌላ ተጨማሪ ቀውስ እና ችግር ውስጥ እንዳይከተን ሁሉም አካላት አመራሮች እና አጋር ድርጅቶች በትብብር ሊሠሩ እንደሚገባም ነው ፕሬዝዳንቷ  አሳስበዋል።

መንግስት የምግብ እና የስርአተ ምግብ ችግሮችን በዘላቂነት በመፍታት ጥራቱ እና ደህንነቱ የተጠበቀ ምግብን ለዜጎች ተደራሽ ለማድረግ የተለያዩ ስራዎችን እየሠራ ያለ ቢሆንም ችግሩን ሙሉ በሙሉ ማስወገድ አልተቻለም ያሉት የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ዛሬ በሚደረገው የምግብ እና ስርዓተ ምግብ የአስር አመት እስትራቴጂ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ጠቃሚ ነው ብለዋል።

የሰቆጣ ቃልኪዳን የ15 አመት ፍኖተ ካርታ ያለው ሲሆን በሶስት ምዕራፍ የተከፈለ ነው:: በሙከራ ጊዜ ትግበራው በአማራ እና በትግራይ ክልሎች ባሉ 40 ወረዳዎች የተከናወነ ሲሆን  ከ2014 ጀምሮ በ200  አዳዲስ  ከፍተኛ መቀንጨር ምጣኔ ባለባቸው ወረዳዎች የሚተገበር መሆኑን የፌዴራል የሰቆጣ ቃልኪዳን ስራ አስፈፃሚ  ዶ/ር ሲሳይ ሲናሞ ገልፀዋል።

በመድረኩ የኢፌዲሪ ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች እና የክልል እና የከተማ አመራሮች ታድመዋል።

(በድልአብ ለማ)