ኢትዮ-ቴሌኮም “የ4 ጂ ኤል ቲ ኢ አድቫንስድ” የኢንተርኔት አገልግሎትን በማዕከላዊ ምዕራብ ሪጅን አስጀመረ

ነሃሴ20/2013(ዋልታ) – ኢትዮ ቴሌኮም በአዲሱ የበጀት አመት የላቀ የኢንተርኔት አገልግሎት መስጠት የሚያስችለውን የአራተኛው ትውልድ “የ4 ጂ ኤል ቲ ኢ አድቫንስድ” የኢንተርኔት አገልግሎትን በማዕከላዊ ምዕራብ ሪጅን አስጀመረ።

ኢትዮ-ቴሌኮም በማዕከላዊ ምዕራብ ሪጅን በሚገኙ የአምቦ፣ሰበታ፣ቡራዩ፣ ሆለታና ወሊሶ ከተማ ነው የ“የ4 ጂ ኤል ቲ ኢ አድቫንስድ” አገልግሎቱን ያስጀመረው።

የኩባንያው ዋና ስራ አስኪያጅ ፍሬህይወት ታምሩ የተለያዩ አካላት በታደሙበት የአምቦ ከተማ መርሀግብር ላይ ተገኝተው የ4ጂ አገልግሎትን አስጀምረዋል። ወይዘሪት ፍሬህይወት ታምሩ በመርሀ ግብሩ ላይ ስለ አራተኛው ትውልድ “የ4 ጂ ኤል ቲ ኢ አድቫንስድ” አገልግሎትና አጠቃቀም ገለፃ አድርገዋል።

ዋና ስራ አስኪያጇ እንዳሉትም “የ4 ጂ ኤል ቲ ኢ አድቫንስድ” ከ3ጂ የተሻለ ፍጥነት፣ ቅልጥፍና እና አስተማማኝ የኢንተርኔት አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ነው ብለዋል። ደንበኞችም አገልግሎቱን ለማግኘት አሁን ከሚጠቀሙበት የ3ጂ የስልክ ቀፎና ሲም ካርድ አጠቃቀም ወደ 4ጂ ቴክኖሎጅ ማስቀየር እንዳለባቸው ተጠቅሷል።

“የ4 ጂ ኤል ቲ ኢ አድቫንስድ” የኢንተርኔት አገልግሎት የሀገሪቱን ምጣኔ ሀብት የሚያሻሽልና የዜጎችን አኗኗር የሚያቃልል  ያሉት የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ስራ አስኪያጅ አገልግሎቱን ወደ ሌሎች ከተሞች የማስፋፋት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በ2013 የበጅት አመት “የ4 ጂ ኤል ቲ ኢ አድቫንስድ” አገልግሎትን በ103 ከተሞች ለማስጀመር ታቅዶ በ5 ወራት ውስጥ 68 ከተሞችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል። በ2014 የበጀት አመት በሚቀጥለው ማስፋፊያም 106 ከተሞችን “የ4 ጂ ኤል ቲ ኢ አድቫንስድ” አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ ስራው ተጀምሯል።

በተያያዘም የቴሌብር አገልግሎትን የማስፋፋት ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል ተብሏል። እስካሁን በቴሌብር 8.9 ሚሊየን ደንበኞችን ለማፍራት የተቻለ ሲሆን። በአዲሱ የበጅት አመት 21 ሚሊዮን የቴሌብር ደንበኞች ለማፍራት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ስራ አስኪያጅ ገልፀዋል።

(በደምሰው በነበሩ)