እስራኤል በኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በንቃት እየተሳተፈች ነው

አምባሳደር አለልኝ አድማሱ

ነሐሴ 28/2013 (ዋልታ) እስራኤል በኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በንቃት እየተሳተፈች መሆኗን በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አለልኝ አድማሱ ገለጹ።

አምባሳደሩ በኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ይፋ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ የእስራኤል ኤምባሲ ዘመቻውን ለመደገፍ በንቃት እየተሳተፈ መሆኑን ተናግረዋል።

የኤምባሲው ሠራተኞችም ዛሬ ከየካ ከፍለ ከተማ ጋር በመተባበር ለምግብነት የሚውሉ የአቦካዶ፣ ሎሚ፣ ብርቱካንና ሌሎችም የፍራፍሬ ችግኞችን መትከላቸውን ገልጸዋል።

አምባሳደር አለልኝ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ይፋ የተደረገው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በኢትዮጵያ ግዙፍ ከሚባሉ ፕሮጀክቶች አንዱ ነው ብለዋል፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ ይፋ የተደረገው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ከተጀመረበት ጀምሮ የእስራኤል ኤምባሲ ዘመቻውን ለመደገፍ በንቃት ሲንቀሳቀስ መቆየቱንም ተናግረዋል።

እንደ ኢዜአ ዘገባ ኤምባሲው መርኃ ግብሩ በስኬት እንዲጠናቀቅ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አምባሳደር አለልኝ አረጋግጠዋል፡፡

ችግኞቹ የተተከሉበትን ፓርክ የፍራፍሬ ምርምር ማዕከል ለማድረግ እቅድ አለን ያሉት አምባሳደሩ፤ ከዩኒቨርሲቲዎችና ከእስራኤል ኤክስፐርቶች ጋር በመተጋገዝ ምርታማነትን ለማሳደግም እንሰራለን ብለዋል።

የየካ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አስፋው ተክሌ የእስራኤል ኤምባሲ በመዲናዋ እየተከናወነ ያለውን የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ለመደገፍ እያሳየ ላለው ቁርጠኝነት አመሰግነዋል፡፡

እስራኤል በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ በአትክልትና ፍራፍሬ ምርት የበለጸገ ልምድ እንዳላት በማስታወስ ከኤምባሲው ጋር የተጀመረው ስራ ልምዱን ወደ ከተማዋ ለማምጣት ያግዛል ብለዋል።

ኤምባሲው በፓርኩ ለመገንባት ያሰበው የምርምር ማዕከል እውን እንዲሆን በቅርበት ለመስራትና አስፈላጊውን እገዛ ለማበርከት ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ዛሬ በትዊትር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ በ2011 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ሲጀመር በአራት ዓመታት 20 ቢሊዮን ችግኞን ለመትከል በማቀድ እንደሆነ አስታውሰዋል።

ባለፉት ሶስት ዓመታት በአጠቃላይ 18 ቢሊዮን ችግኝ መትከል እንደተቻለም ገልጸዋል።