አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ከሶማሌላንድ ፕሬዚዳንትጋር ተወያዩ

አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን

ነሐሴ 28/2013 (ዋልታ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ከሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ባሂ አብዲ ጋር ተወያይተዋል።

ሁለቱ ወገኖች በድንበር አካባቢ ስላለው የፀጥታ እና የፍልሰት ጉዳዮች እንዲሁም በኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ መካከል የባህል ግንኙነትን ማጠናከር እና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስ በሚቻልበት መንገድ ላይ መመካከራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር  ገልጿል፡፡

በተመሳሳይ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ከሶማሊላንድ ተጠባባቂ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሊበን ዩሱፍ ጋር ባደረጉት ውይይት የኮቪድ-19 ገደቦችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ በውጫሌ ድንበር የኢሚግሬሽን አገልግሎት ዳግም በሚጀመርበት ሁኔታ ላይ መክረዋል።

ለሁለት ቀናት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት በትላንትናው ዕለት ሶማሊላንድ የገቡት አምባሳደር ሬድዋን፣ ከሶማሊላንድ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን በርበራ ወደብ ኮሪደርን መጎብኘታቸውም ተገልጿል።

ከሳሂል ክልል አስተዳዳሪ አህመድ ኦስማን እና ከበርበራ ከንቲባ አብዲሻኩር ሞሐሙድ ጋር ባደረጉት ውይይት፣ ሶማሊላንድ የኢትዮጵያ የኤክስፖርት ምርቶች መዳረሻ የመሆን አቅም ያላት መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የበርበራ ወደብ ኮሪደርን በመጠቀም ከሶማሊላንድ ጋር ያላትን የኢንቨስትመንት እና የቱሪዝም ተሳትፎዋን በማሳደግ የኢኮኖሚ ትስስሯን ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ የማድረግ ፍላጎት እንዳላት አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ገልጸዋል።