ኢመደኤ እና አሪፍፔይ በዲጂታል ክፍያ ሥርዓት ላይ በጋራ ለመስራት ተፈራረሙ

ታኅሣሥ 7/2014 (ዋልታ) የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) እና አሪፍፔይ የዲጂታል ክፍያ ስርአት ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸዉን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ።

በመግባቢያ ስምምነቱ ላይ የተገኙት በኢመደኤ የደራሽ የዲጂታል ክፍያ ፕላትፎርም ዳይሬክተር ብሩክ ወልደየስ ኤጀንሲው ኅብረተሰቡን ይጠቅማሉ ባላቸው ጉዳዮች ከመንግስታዊም ሆነ መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በመተበበር እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡

ከአሪፍፔይ ጋር የተደረሰዉ ስምምነት አንዱ ማሳያ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

የአሪፍፔይ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሃብታሙ ታደሰ በበኩላቸዉ ኩባንያቸው ከደራሽ ፕላትፎርም ጋር በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ መድረሳቸዉ ከ90 ከመቶ በላይ ግብይት እየተደረገበት ያለዉን የጥሬ ገንዘብ ልዉዉጥ ጥገኝነትን ይቀንሳል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ደንበኞች ከተለያዩ ተቋማት ላገኙት አገልግሎት ክፍያዎችን በተቀላጠፈና ደህንነቱ በተጠበቀ መንገድ በቀላሉ ለመክፈል ያስችላቸዋልም ብለዋል፡፡

አሪፍፔይ ፋይናንሽያል ቴክኖሎጂ መሆኑን እና አንድ ተጠቃሚ አካዉንቱን ከአሪፍፔይ መተግበሪያ ጋር ሊንክ በማድረግ ባለበት ቦታ ሆኖ የውኃ፣ መብራት፣ ትምህርት፣ ታክሲ፣ ሱፐር ማርኬትና ሌሎች የግብይት አገልግሎቶችን ለመፈጸም ያስችላል መባሉን ከኤጀንሲው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ደራሽ የዲጂታል ክፍያ ፕላትፎርም ከ16 ባንኮች ከ10 ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ጋር በትብብር እየሰራ ይገኛል፡፡