የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ለ12ኛ ጊዜ ዛሬ ይወያያል

ታኅሣሥ 11/2014 (ዋልታ) የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ለ12ኛ ጊዜ ዛሬ ውይይት ያደርጋል።
ዩናይትድ ኪንግደም፣ አሜሪካ፣ አየርላንድ፣ ፈረንሳይ፣ ኖርዌይና ኢስቶኒያ ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ እንዲወያይ ጥያቄ ያቀረቡ አገራት ናቸው።
በስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ኢንስቲትዩት የዓለም ዐቀፍ ግንኙነት ተመራማሪ ሄኖክ ጌታቸው (ዶ/ር) ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት አስተያየት የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የሚያካሄደው ተደጋጋሚ ስብሰባ አንዳንድ ምእራባዊያን አገራት ድርጅቱን ለፖለቲካ ፍላጎታቸው መጠቀሚያነት እንዳደረጉት ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
የመጨረሻ ግቡም እነዚህ አገራት ኢትዮጵያን በማዳከም ካላት መልክዓ-ምድራዊ አቀማመጥ የሚመነጩ የፖለቲካ ፍላጎቶቻቸውን ማሳካት መሆኑንም ተናግረዋል።
አገራቱ በኢትዮጵያ ላይ የፖለቲካ ፍላጎታቸውን ለመጫን የተባበሩት መንግስታትን ጨምሮ ሌሎች ዓለም ዐቀፍ ተቋማትን እንደ ፖለቲካ መሳሪያ እየተጠቀሙ መሆኑን አመልክተዋል።
“የተባበሩት መንግስታት እ.አ.አ በ1945 የተመሰረተው የሁለተኛው የዓለም ጦርነት አሸናፊ አገራትን ፍላጎት መሰረት አድርጎ መሆኑን” ነው ተመራማሪው ያስረዱት።
ድርጅቱ ላለፉት ሰባት አስርት ዓመታት የተወሰኑ ኃያላን አገራት የፖለቲካ ፍላጎት ማስጠበቂያ ሆኖ መቆየቱንም ተናግረዋል።
ከ190 በላይ አባል አገራትን ያቀፈው የተባበሩት መንግስታት እየተከተለ ያለው አሰራር በዓለም ላይ ያሉ አሁናዊ የፖለቲካ ለውጦችን የማይወክል ነው ማለታቸውን የኢዜአ ዘገባ አመልክቷል፡፡
ተቋሙ በዓለም ላይ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ቢቋቋምም አሁን ላይ በተቃራኒ መንገድ እየሄደ እንደሚገኝ እና የጸጥታው ምክር ቤት ከዚህ ቀደም በአፍሪካና በሌሎች አገራት ያሳለፋቸው ውሳኔዎች አገራቱን አለመረጋጋት ውስጥ በመክተት ለችግር መዳረጉን አመልክተዋል።
አንዳንድ ምዕራባውያን አገራት ምክር ቤቱን በመጠቀም በኢትዮጵያ ላይ ተመሳሳይ ድርጊት ለመፈጸም እየሰሩ እንደሆነም አብራርተዋል።
በመሆኑም ድርጅቱ ከወገንተኝነት የፀዳ እንዲሆን የሚያስችሉ የአሰራር ማሻሻያዎች ያስፈልጉታል ነው ያሉት፡፡
ማሻሻያዎቹም የዓለም አሁናዊ የፖለቲካ ሁኔታን ያገነዘቡና የዓለም አገራት ድምጽ ፍትሐዊ በሆነ መልኩ እንዲሰሙ የሚያደርጉ መሆን እንዳለባቸውም ገልጸዋል፡፡
አፍሪካን ጨምሮ በጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ የሌላቸው አህጉራትን ያማከሉ መሆን እንደሚጠበቅባቸውም እንዲሁ፡፡
የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሐፊ የነበሩት ኮፊ አናንን ጨምሮ ብራዚል፣ ጃፓን፣ ሕንድና ጀርመን ድርጅቱ አሁን ያለውን የፖለቲካ ነባራዊ ሁኔታ ያማከለ ማሻሻያ እንዲያደርግ ጥረት ሲያደርጉ እንደነበረም አስታውሰዋል።
እንቅስቃሴው አሁን ላይ ዳግም መቀስቀሱንና ጥያቄውን በተደራጀ መልኩ ማካሄድ የሚያስችል የተቀናጀ ስትራቴጂ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።