ከዳያስፖራው ለሚላኩ ጤና ነክ ድጋፎች በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ጊዜያዊ ማከማቻ መዘጋጀቱ ተገለጸ

ዶክተር ሊያ ታደሰ

ታኅሣሥ 11/2014 (ዋልታ) ከኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ለሚላኩ ጤና ነክ ድጋፎች በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም ዐቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጊዜያዊ ማከማቻ ቦታ መዘጋጀቱን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በሕወሓት የሽብር ቡድን ጥቃት በአማራ እና በአፋር ክልሎች የወደሙ የጤና ተቋማትን መልሶ ለመገንባት እና ለማቋቋም ጥረት መጀመሩ እና የተለያዩ ግብዓቶችን በመላክ ጭምር ይህን ጥረት ለማገዝ ዳያስፖራው እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡

እነዚህን ግብዓቶች በጊዜያዊነት ለማከማቸት የሚያስችል ቦታ የጤና ሚኒስቴር ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም ዐቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ማዘጋጀቱን ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ አስታውቀዋል፡፡

በዚህ ዙሪያ ዝርዝር መረጃ ማግኘት የሚሹ ግለሰቦችም ይሁኑ ተቋማት በጤና ሚኒስቴር የተዘጋጀውን የልገሳ መመሪያ እና ቅድሚያ የሚሰጣቸው የጤና ግብዓቶች ዝርዝር መመልከት የሚችሉ መሆኑን ሚኒስትሯ በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት አመለክተዋል፡፡