ለሽብር ቡድኖቹ ሕወሓትና ሸኔ ዓላማ ሊውል የነበሩ ቁሶችና 164 ተጠርጣሪዎች ተያዙ

ታኅሣሥ 12/2014(ዋልታ) በሕገ ወጥ መንገድ ከኢትዮጵያ ሊወጡ የነበሩ የተለያዩ አገራት ገንዘቦች እና 5 ነጥብ 8 ኪሎ ግራም ጥፍጥፍ ወርቅ እንዲሁም ለሕወሓት እና ለሸኔ የሽብር ዓላማ ማስፈጸሚያ በድብቅ ሊተላለፉ የነበሩ የግንኙነት መሣሪያዎች እና አልባሳት ከ164 ተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለፀ።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙኃን በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፤ ከወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ በቦሌ ኤርፖርት በተደረገ ጥብቅ ክትትልና ፍተሻ በተፈጨ ስጋ ተጠቅልለው በሕገ ወጥ መንገድ ከሀገር ውጭ ሊወጡ ሲሉ የተያዙትን 34 ሺሕ 100 ፓውንድ፣ 27 ሺሕ 170 ዩሮ ፣ 6 ሺሕ 200 የስዊዝ ፍራንክ እና 400 የካናዳ ዶላርን ጨምሮ 4 ሚሊዮን 59 ሺሕ 378 የኢትዮጰያ ብር፣ 209 ሺሕ 750 የአሜሪካ ዶላር፣ 47 ሺሕ 370 ዩሮ እና 37 ሺሕ 330 የእንግሊዝ ፓውንድ በወንጀሉ ከተጠረጠሩ 134 ግለሰቦች ጋር በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡

5 ነጥብ 8 ኪሎግራም ጥፍጥፍ ወርቅም በሕገ ወጥ መንገድ ከኢትዮጵያ ሊወጣ ሲል የተያዘ ሲሆን፤ ከሕገ ወጥ ድርጊቱ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የተጠረጠሩ 12 ግለሰቦች ተይዘው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑ ተገልጿል፡፡

መግለጫው እንዳብራራው በሕገወጥ መንገድ ወደ ውጭ ሊወጡ የነበሩ የተለያዩ አገራት ገንዘቦች በአሸባሪነት ለተፈረጁት ሕወሓትና ሸኔ የውጭ ሴሎች የፋይናንስ አቅርቦት በማሟላት በኢትዮጵያ የሽብር ተግባር እንዲፈጸም እና የውጭ ምንዛሪ በማሸሽ የአገር ምጣኔሃብትን ለማዳከም የሚውሉ ነበሩ፡፡

በተያያዘም በአሸባሪነት የተፈረጁት ሕወሓት እና ሸኔ ለመፈጸም ላቀዱት የሽብር ተግባር እንዲውሉ ታቅደው በድብቅ ሊተላለፉ የነበሩ የግንኙነት መሣሪያዎች እና አልባሳት ሰሞኑን በተከታታይ በተደረጉ ክትትሎችና ፍተሻዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታውቋል፡፡

አሸባሪዎቹ ሕወሓት እና ሸኔ ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር ጭምር በማበር አገር የማፍረስ የውክልና ጦርነት ላይ ቢሰማሩም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሚመራው የኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች ሽንፈት እየተከናነቡ በመሆኑ በግንባር ያጡትን ውጤት የተለያዩ ስልቶችን በመጠቀም የሽብር ተግባር በመፈጸም ለማካካስ ጥረት እያደረጉ መሆኑን የጠቆመው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት መግለጫ፤ የአሸባሪ ቡድኖቹን ህቡዕ እንቅስቃሴና

የግንኙነት መረብ በመከታተል በተደረገው ጥብቅ ክትትል 13 የጂፒኤስ መሣሪያዎች፣ 9 ሳተላይት የመገናኛ ሬዲዮኖች፣5 ሳተላይት ስልኮች፣ የጦር ሜዳ መነፀር እና አልባሳት ለህወሓትና ለሸኔ የሽብር ተልዕኮ ማስፈጸሚያነት ወደ ሀገር ውስጥ ሊገቡ ሲሉ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን፤ በድርጊቱ የተጠረጠሩ አምስት ግለሠቦችም በጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየተጣራ ይገኛል፡፡

የሽብር ቡድኖቹ ‹‹አዲስ አበባን ከበናል፤ በጥቂት ቀናትም በቁጥጥር ስር እናውላታለን›› በማለት በዓለም ዐቀፍ መገናኛ ብዙኃን ጭምር የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ሲነዙ እንደነበር ያስታወሰው መግለጫው ለዚህ ተልዕኮ እንዲውሉ ታቅደው ወደ ከተማዋ በተለያዩ ስልቶች ሊገቡ የነበሩ አልባሳቶች መያዛቸውን አስታውቋል፡፡

የሽብር ቡድኖቹ የውጭ ሴሎች በፖስታ ቤት ከተለያዩ ልብሶች ጋር በመቀላቀል የሸኔና የተቃዋሚ አመራሮች ምስል ያለባቸው ልብሶች እንዲሁም የአነግ አርማ የታተመባቸው ቲሸርቶች፣ ኮፍያዎችና የአንገት ፎጣዎችን፤ በተመሳሳይም የአሸባሪው ህወሓት አመራሮች ምስልና አርማ የታተሙባቸውን ቲሸርቶች በፖስታ ቤት በመላክ ለማስገባት ሙከራ ቢያደርጉም በተከናወነው ጥብቅ ክትትል መያዛቸውን ያመለከተው መግለጫው፤250 የሚሆኑ የወታደር የሚመስሉ ልብሶችና ኮፍያዎችም በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ ሊገቡ ሲሉ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጠቁሟል፡፡ ከሕገወጥ ድርጊቱ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የተጠረጠሩ 13 ሰዎችም ተይዘዋል፡፡

እነዚህ አልባሳት ወደ አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ ለአሸባሪ ቡድኖቹ ተላላኪዎችና ናፋቂዎች ተሰራጭተው እንዲለብሱትና በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ፎቶ ተነስተው በማኅበራዊ ትስስር ገጾች እንዲለቁት በማድረግ ‹‹አዲስ አበባን ተቆጣጥረናል›› የሚል የሀሰት ፕሮፓጋንዳ እና የስነ ልቦና ጦርነት ለማካሄድ ታልሞ እንደነበር የጠቆመው መግለጫው፤ እቅዱ የመረጃና የደኅንነት ተቋሙ ከጸጥታ ኃይሎች ጋር ባከናወነው ኦፕሬሽን ከውጥኑ መምከኑን አስታውቋል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በላከው መግለጫ እንዳመለከተው ከወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ በአሸባሪነት የተፈረጁ ቡድኖችን ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ ለመግታት ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ ሲሆን፤ ኅብረተሰቡም እየተገኘ ላለው ውጤት ወሳኝ ሚና እያበረከተ ይገኛል፡፡ ወደፊትም ኅብረተሰቡ አጠራጣሪ ነገሮችን ሲመለከት በአካባቢው ለሚገኙ የጸጥታና ደኅንነት አካላት ጥቆማ በመስጠት ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ጥሪ አቅርቧል፡፡