ለኢትዮጵያውያን የአብሮነትና መደጋገፍ እሴት መጎልበት ሁሉም በኃላፊነት ሊሰራ እንደሚገባ ተገለፀ

ታኅሣሥ 12/2014(ዋልታ) የኢትዮጵያውያን የአብሮነትና የመደጋገፍ እሴት እንዲጠናከር ሁሉም በኃላፊነት መንፈስ እንዲሰራ የደቡብ ክልል የሀገር ሽማግሌዎች አሳሰቡ።

ከክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት አባቶች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ዙሪያ ከደቡብ ክልል ርእሰ መስተዳደር ርስቱ ይርዳው ጋር  ዛሬ በሆሳዕና ከተማ ተወያይተዋል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች እንደገለጹት፤ ባለፉት 27 ዓመታት አሸባሪው ህወሓት በሀገሪቱ የነበሩ የአንድነትና አብሮነት እሴቶችን ለመሸርሸር ሲሰራ ቆይቷል።

አሁን ያለው አገራዊ የለውጥ ምዕራፍ ዘላቂ እንዲሆንና የኢትዮጵያውያን የአብሮነትና የመደጋገፍ እሴት እንዲጎለብት ሁሉም በኃላፊነት መንፈስ እንዲሰራ አሳስበዋል።

አሸባሪው ህወሓት በከፈተው ጦርነት የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋምና ወደ ቀደመ የተረጋጋ ህይወታቸው እንዲመለሱ በሚደረገው ጥረት ሁሉም አካል ባለው አቅም ከጎናቸው ሊቆም ይገባል ብለዋል።

አገራዊ አንድነትን አጠናክሮ ለማስቀጠልና አሸባሪው ህወሓት በከፈተው ጦርነት ሳቢያ የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ሁሉን አቀፍ ጥረት ያልተቆጠበ ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል።

በክልሉ የሚገኙ የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች አገራዊ አንድነትን በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ መምከራቸው ፋይዳው የጎላ እንደሆነም ተሳታፊዎቹ ገልጸዋል፡፡

በአሸባሪው ህወሓት አማካኝነት የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን ጉዳይ የሁላችንም ጉዳይ በመሆኑ ዜጎችን መልሶ በማቋቋም ወደ ነበረው ሰላማዊ እንቅስቃሴያቸው እንዲመለሱ የማድረግ ግዴታ አለብን ብለዋል።

”እኛ ኢትዮጵያውያን የውስጥ ችግራችንን ለማንም አሳልፈን የማንሰጥና ራሳችንን በራሳችን በመደገፍ የምንታወቅ ህዝቦች ነን” ሲሉ በአፅንኦት ተናግረዋል።

ወገኖቻችንን መልሶ በማቋቋም ወደ ነበሩበት ሰላማዊ ህይወት የመመለስ ኃላፊነት ለሌላ የምንተወው ጉዳይ አይደለም ሲሉም አረጋግጠዋል።

የደቡብ ክልል  ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ እንዳሉት የሀገሪቱን አኩሪ ባህልና እሴቶች በማስቀጠል ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ሚና ከፍትኛ ነው።

ይህንን ሚናቸውን በመጠቀም ህብረተሰቡን በማስተባበር የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው እንቅስቃሴ ከመንግሥት ጎን እንዲቆሙ ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ለዜጎች ሁለንተናዊ እድገትና ብልፅግና መንግሥት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል።