22 ፓርቲዎች በአማራና አፋር ክልሎች የወደሙ 4 የማኅበራዊ ተቋማትን ሊገነቡ ነው

ታኅሣሥ 20/2014 (ዋልታ) በአዲስ አበባ የሚንቀሳቀሱ 22 የፖለቲካ ፓርቲዎች በአማራ እና አፋር ክልሎች የወደሙ አራት የማኅበራዊ ተቋማትን ሊገነቡ መሆኑን የፓርቲዎች ጥምረት ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ አስታወቀ።

በእያንዳንዱ ዘርፍ ኮሚቴ አዋቅሮ የወገንን ኃይል ሲደግፍ መቆየቱን የጥምረቱ ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ እና የኢሕአፓ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ መጋቢ ብሉይ አብርሃም ሃይማኖት ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም በደሴ ግንባር በመገኘት ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ቁሳቁስ ድጋፍ ለወገን የፀጥታ አካላት ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል።

እቅዱ በአማራና አፋር ክልሎች በእያንዳንዳቸው አንድ ሆስፒታልና አንድ ትምህርት ቤት በድምሩ አራት ተቋማትን መልሶ መገንባት ሲሆን በአገር ውስጥና በውጭ ያሉ የፓርቲዎቹ ደጋፊዎች የሀብት ማሰባሰብ እንቅስቃሴውን በብርቱ ደግፈው እያገዙ መሆኑም ገልጸዋል።