የፌደራል መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች የ3 ቀን ውይይት ተጀመረ

ታኅሣሥ 21/2014 (ዋልታ) የፌደራል መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ መወያየት ጀመሩ፡፡

ብልፅግና ፓርቲ ተገደን የገባንበት የኅልውና ጦርነት የመጀመሪያ ምዕራፍ በድል ተጠናቋል ብሏል፡፡

ለ3 ቀናት የሚቆየው ውይይትም የተገኙትን ሁለንተናዊ ድሎች ጠብቆ የማስፋትና ወደ ዘላቂ ሰላምና ልማት ማሸጋገር ላይ ያተኮረ ይሆናል ተብሏል፡፡

የተገኘውን ድል ተከትሎ ሊመጡ የሚችሉ ፖለቲካዊ፣ ምጣኔሃብታዊ፣ ሰብኣዊና የፀጥታ ፈተናዎችን በብቃት መፍታትና በአግባቡ መምራትም እኩል ትኩረት ያገኛሉ ነው ያለው፡፡

‹‹በኅልውና ጦርነት ሂደት ውስጥ ያገኘናቸው አገራዊ አንድነት ተናቦና ተቀናጅቶ የመስራት ልምድ በጋራ ዓላማ ለጋራ የመስራት ልምድ የአመራር ሁለንተናዊ ተሳትፎና ቁርጠኝነት ለአገራችን ዘላቂ ሁለንተናዊ ብልፅግና ለመጠቀም በሚያስችል መልኩ የመምራት አስፈላጊነት ላይ ከፍተኛ አመራሩ በጥልቀት ይወያያል›› ሲልም አክሏል፡፡

በውይይቱ የድኅረ ጦርነት ፖለቲካዊ፣ ምጣኔሃብታዊ የፀጥታና ሰብኣዊ ሁኔታዎች በብቃት በመምራት የሚያስችሉ አቅጣጫዎች ይቀመጣሉ ተብሎም እንደሚጠበቅ ነው ከብልፅግና ፓርቲ ያገኘነው መረጃ የሚጠቁመው፡፡