የሚኒስቴሮች 100 ቀናት የእቅድ አፈጻጸም ግምገማ ጠ/ሚ ዐቢይ በተገኙበት በጉባ እየተካሄደ ነው  

ታኅሣሥ 27/2014 (ዋልታ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የሚኒስቴሮች የ100 ቀናት አፈጻጸም የግምገማ መድረክ ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ በሚገኝበት ጉባ እየተካሄደ ነው፡፡

በመድረኩ ላለፉት ሳምንታት የተቋማቱን አፈጻጸም በተለያየ የቁጥጥር ሥርዓቶች ሲከታተል የቆየው የፕላንና ልማት ሚኒስቴር የእያንዳንዱን ሚኒስቴር ተቋማት አፈጻጸምን አቅርቧል፡፡

የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) እንዳሉት ሀገሪቱ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ብታልፍም ባለፉት 100 ቀናት በዋና ዋና የማክሮ ኢኮኖሚ ዘርፎች ጥሩ ውጤት ተመዝግቧል።

ባለፉት 100 ቀናት በግብርናው ዘርፍ የመኸር ምርት መሰብሰብ እና የመስኖ ዝግጅት ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።

ከወጪ ንግድም በ100 ቀናት ውስጥ ከ800 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱንም የፕላን እና ልማት ሚኒስትሯ ባቀረቡት ሪፖርት ገልጸዋል።

ኢኮኖሚው በማክሮ ደረጃ ጥሩ ውጤት እንደተመዘገበበት ቢገመገምም ሀገሪቱ ተገዳ በገባችበት ጦርነት ምክንያት ከፊቱ በርካታ ፈተናዎች እንደተደቀኑበት ሚኒስትሯ በግምገማ መድረኩ ላይ መናገራቸውን ኢብኮ ዘግቧል።

በታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ የተጀመረው የፌዴራል ተቋማትን የሚመሩት ሚኒስትሮች ስብሰባ ሁልጊዜ ከሚካሄድበት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ወጣ ብሎ ሲካሄድ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን ከዚህ በፊት በኮይሻ መካሄዱም የሚታወስ ነው።