መንግሥት የትግራይ ሕዝብ አሸባሪውን ትሕነግ በአደባባይ ወጥቶ ሊቃወመው ይገባል አለ

ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)

ታኅሣሥ 27/2014 (ዋልታ) መንግሥት የትግራይ ሕዝብ ያለበት ማኅበራዊና ምጣኔሃብታዊ ችግር ተፈቶ በዘላቂነት ሰላሙ እንዲረጋገጥ አሸባሪውን ትሕነግ ማውገዝ ብቻ ሳይሆን በአደባባይ ወጥቶ ሊቃወመው ይገባል አለ፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) የትግራይ ሕዝብ አሸባሪው ትሕነግ በጦርነት ብቻ የመኖር ፍላጎት እንዳለው በመገንዘብ ሊያስቆመው ይገባል ብለዋል።

በኢትዮጵያም ይሁን በውጭ አገራት የሚኖር የትግራይ የተማረው የኅብረተሰብ ክፍል የሽብር ቡድኑን እኩይ ሴራ በማሳወቅ ሕዝቡን ሊያነቃ ይገባልዋልም ነው ያሉት።

መከላከያ ወደ ትግራይ መግባቱን ትቶ ባለበት እንዲፀና የተደረገው የትግራይ ሕዝብ በድጋሚ የማስተዋል ጊዜ እንዲያገኝ በማሰብም ጭምር መሆኑን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል አሸባሪው ትሕነግ በከፈተው ጦርነት የተጎዱ የማኅበረሰብ ክፍሎችና አካባቢዎችን መልሶ የማቋቋም ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።

መላው ኢትዮጵያዊ ለመልሶ ማቋቋሙ ድጋፍ እንዲያደርግ የጠየቁት ሚኒስትሩ የቴሌኮም፣ የኤሌትሪክ፣ የባንክ ና መሰል አገልግሎቶች ወደ ሥራ መመለሳቸውን ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ በሰጡት መግለጫ የኢትዮጵያ አየር መንገድም ወደ ላሊበላና ኮምቦልቻ በረራ መጀመሩን አንድ እምርታ ሲሉም አንስተዋል፡፡

በመስከረም ቸርነት