የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

ታኅሣሥ 28/2014 (ዋልታ) የአማራ፣ ደቡብ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሣነ መስተዳድሮች የገና በዓልን አስመልክቶ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች ለገና በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ርዕሠ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) በዓሉ የደስታና የመሠባሠቢያ ወቅት እንደመሆኑ ወደቀያቸው የተመለሱ ዜጎች የመፅናኛ በዓል እንዲሆንላቸው በመደጋገፍ ልናከብረው ይገባል ብለዋል።

በዓሉን ስናከብር ከተረፈን ሳይሆን ካለን ቀንሰን ለክልሉ መልሶ ግንባታ በማዋልና፣ የተፈናቀሉ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም የሚያስችል ድጋፍ በማድረግ ሊሆን እንደሚገባም አሳስበዋል።

የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እርስቱ ይርዳው ባስተላለፉት እንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸው ኢትዮጵያ በውስብስብ ፈተናዎች ውስጥ አልፋ ወደ ትንሣኤዋ እያመራች ባለችበት ወቅት መሆኑ በዓሉን ልዩ እንደሚያደርገው ገልጸዋል።

ሙሉ ትኩረታችን በድህረ ጦርነት የሚያጋጥሙንን ችግሮች ተጋፍጠን የኢትዮጵያን ትንሳዔ ከፍ ማድረግ ነው ብለዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በቁርጥ ቀን ልጆቿ ተጋድሎ አሁን ያገኘችውን ድል የበለጠ በመቀዳጀት፣ ሰላምና አንድነትን ጠብቆ ማቆየት እንደሚገባ በእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸው አሳስበዋል፡፡

ሰላምና ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትን ለማስከበር ሲሉ ዝናብና ጸሐይ ሳይበግራቸው በተለያዩ ግንባሮች ላይ ተሰማርተው የሕይወት መስዋዕትነት እየከፈሉ ለሚገኙ የሠራዊት አባላት መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡