አሸባሪው ሸኔ የሻምቡ ባኮን የአስፓልት ኮንክሪት መንገድ መቆራረጡ ተገለፀ

የሻምቡ ባኮን የአስፓልት ኮንክሪት መንገድ

ጥር 3/2014 (ዋልታ) አሸባሪው ሸኔ የሆሩ ጉዱሩ ወለጋ ዞንን ከምዕራብ ሸዋ እና ምስራቅ ወለጋ ዞን ጋር የሚያገናኘውን የሻምቡ ባኮን ብቸኛ የአስፓልት ኮንክሪት መንገድ በመቆራረጥ የትራንስፖርት ሂደቱ ላይ እንቅፋት መሆኑ ተገለፀ።

የሆሩ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አስተዳዳሪ በቀለ ደቻሳ እንደሚሉት ቡድኑ አጠቃላይ የፈፀመውን ጥፋት የመለየት ስራ እየተሰራ ቢሆንም ሸኔ በሕዝቦች ላይ ያደረሰው ጉዳት ቀላል የሚባል አይደለም።

አሸባሪው ሸኔ አንቡላንሶችን ጨምሮ ሌሎች የሕዝብ አገልግሎት ሰጭ ተሽከርካሪዎችን ያለርህራሔ ማውደሙን ገልፀው በዞኑ በሚገኙ 13 ወረዳዎች ላይ ቀላል የማይባል ውድመት ፈፅሟል ብለዋል።

የሻምቡ ባኮን የአስፓልት ኮንክሪት መንገድ ከ 60 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያለው ሲሆን በተለያዩ ስፍራዎች አሸባሪው ሸኔ ቆራርጦ የትራንስፖርት እንቅስቃሴውን ለማስተጓጎል ጥረት ማድረጉም ተገልጿል።

በቅርቡ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት የሆነው የሻምቡ ባኮ የአስፓልት ኮንክሪት መንገድ በዞኑ ብቸኛው የአስፓልት መንገድ ቢሆንም የሽብር ቡድኑ ሸኔ ቆራርጦታል። ሸኔ ከጁንታው የሚሰጠውን ተልዕኮ የሚያስፈፅም ኃይል መሆኑን ሕዝባችን ተገንዝቦ ቡድኑን ለማጥፋት አቋም ይዞ እየታገለው ነው ሲሉ የዞኑ አስተዳዳሪ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሻምቡ ባኮን የአስፓልት ኮንክሪት መንገድ ከወራት በፊት ማለትም የካቲት 14/ 2013 ዓ.ም በሆሮ ጉዱሩ ዞን ሻምቡ ከተማ ተገኝተው በይፋ መርቀው ስራ ማስጀመራቸው ይታወቃል።

ደረሰ አማረ (ከሻምቡ)