በአማራ ክልል የሚተገበር የ4.5 ቢሊዮን ብር ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ

ጥር 2/2014 (ዋልታ) የአማራ መልሶ መቋቋምና ልማት ድርጅት (አመልድ) በአማራ ክልል የሚተገበር የአምስት ዓመታት ፕሮጀክት ስምምነት ተፈራርሟል፡፡

አመልድ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ አደጋ በሚያጋጥም ጊዜ የዕለት ደራሽ ድጋፍ በማድረግ፣ በመልሶ ማቋቋም እና በልዩ ልዩ የልማት ሥራዎች አማራ ክልልን የሚደግፍ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ነው፡፡

ድርጅቱ ከለጋሽ አካላት ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ አማካኝነት ለአምስት ዓመታት የሚተገበር የ4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ስምምነት ዛሬ ተፈራርሟል፡፡

የፕሮጀክቱ መዳረሻ የኅብረተሰቡን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል ሲሆን ትኩረቱንም የመተዳደሪያ አቅምን በማሳደግ፣ የአመጋገብ ስርዓትን በማሻሻል እና የተቋማትን አቅም በማጎልበት ላይ አድርጎ እንደሚሰራ አሚኮ ዘግቧል፡፡

በሰሜን ወሎ ዞን እና በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በሚገኙ ዘጠኝ ወረዳዎች ነው ተግባራዊ እንደሚደረግና በ207 ቀበሌዎች 217 ሺሕ 879 ሰዎች ቀጥተኛ ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ተገልጿል፡፡

የአመልድ ዋና ዳይሬክተር ዓለማየሁ ዋሴ (ዶ/ር) ‹‹ፕሮጀክቱ የሚተገበርባቸው ወረዳዎች አሸባሪው የሕወሓት ወራሪ ቡድን ጉዳት ያደረሰባቸው በመሆኑ በተለዬ የታሪክ አጋጣሚ ለድርጅቱ ትልቅ ፕሮጀክት ነው›› ብለዋል፡፡