ጄኔራል ባጫ ደበሌ ሕዝባችን የጀግንነታችን ምንጭ ነው አሉ

ጥር 6/2014 (ዋልታ) “ሕዝባችን የጀግንነታችን ምንጭ ነው” ሲሉ በመከላከያ ሚኒስቴር የሰራዊት ግንባታ ስራዎች ዋና አስተባባሪ ጄኔራል ባጫ ደበሌ ተናገሩ።

የዳያስፖራ አባላት ለተሰው እና ለቆሰሉ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ልጆች ትምህርት ቤት ለማስገንባት ውይይት ተካሂዷል፡፡

በውይይቱ ጦርነቱን ለመመከት በውስጥም በውጭም ያሉ ኢትዮጵያዊያን “ኢትዮጵያ አትበተንም” በማለት በጋራ ቆመው ድል ማድረጋቸውን ጄኔራል ባጫ ገልጸዋል።

ዳያስፖራው በዲፕሎማሲና በኢኮኖሚ ግንባር እየተዋጋ አኩሪ ስራ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው ይህን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በተለይ ለተሰውና ለቆሰሉ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ልጆች ትምህርት ቤት አቋቁሞ መደገፍ አስፈላጊና ተገቢ በመሆኑ ስራውን ቶሎ መጀመር እንደሚገባ አሳስበዋል።

የቀድሞ ጦር ሰራዊት አባልና የብሔራዊ ጀግኖች እና ህጻናት አምባ ማኅበር የቦርድ አባል ብርጋዴር ጄኔራል ካሳዬ ጨመዳ በበኩላቸው “ኢትዮጵያዊያን አንድ ላይ ከቆምን የውጭ ጠላቶችም ሆነ የሚጋለቡት ፈረሶች አይደፍሩንም” ብለዋል።

የዳያስፖራ አባላት የመጣነው ብሔራዊ ግዴታችንን ለመወጣት በመሆኑ በሚያስፈልገው ሁሉ የበኩላችንን ለማድረግ ቁርጠኞች ነን ሲሉ ገልጸዋል።