በድርቅ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ፈጣን ምላሽ መስጠት እንደሚገባ ተገለጸ

ጥር 6/2014 (ዋልታ) በድርቅ አደጋ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት በትኩረት መስራት እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አሳሰቡ፡፡
የብሔራዊ አደጋ መከላከል እና ዝግጁነት ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል።
በስብሰባውም በአስቸኳይ ጊዜ የድጋፍ አሰጣጥ ሂደት አስፈፃሚ አካላት ያሳዩት ፈጣን ምላሽ እና ቅንጅታዊ አመራር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
የብሔራዊ አደጋ መከላከል እና ዝግጁነት ኮሚቴ ሰብሳቢው ደመቀ መኮንን ኮሚቴው ባስቀመጠው አቅጣጫ በአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ አቅርቦት እና ስርጭት ሂደት ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮችን ዘላቂ በሆነ መልኩ በመፍታት በድጋፍ ምላሹ የመጨረሻ ተጠቃሚዎችን ማዕከል ማድረግ ይገባል ብለዋል።
የብሔራዊ አደጋ መከላከል ኮሚሽን ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ከገጠማት ውስብስብ ችግሮች አኳያ ከአጋር አካላት የሚደረገው ድጋፍ በቂ በሚባል ደረጃ ባለመሆኑ ምክንያት ጅምር የድጋፍ እና ምላሽ አሰጣጥ ሂደቱ ላይ አሉታዊ ጫና እየፈጠረ እንደሚገኝ መግለጻቸውን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ አመላክቷል።