በአፍሪካ የሚደረግን ማንኛውም ኢ-ሕገ መንግሥታዊ የመንግሥት ለውጥ ሁሉም ልያወግዘው ይገባል ተባለ

ጥር 28/2014 (ዋልታ) በአፍሪካ የሚደረግን ማንኛውም ኢ-ሕገ መንግሥታዊ የመንግሥት ለውጥ ሁላችንም ልናወግዘው ይገባል ሲሉ ተሰናባቹ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ፌሊክስ ሺሲኬዲ ጥሪ አቀረቡ።

የአፍሪካ ኅብረት ሊቀ መንበር በመሆን ለአንድ ዓመት የመሩት የዲሞክራቲክ ረፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ሺሲኬዲ ሃላፊነታቸውን የወቅቱ ሊቀመንበር ሆነው ለተመረጡት የሴኔጋሉ ፕሬዝዳነት ማኪ ሳል አስረክበዋል።
ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ሺሲኬዲ በስንብት ንግግራቸው ኅብረቱን በሊቀመንበርነት በመሩበት ቆይታቸው የነበራቸውን ክንውን ጠቅሰዋል።
ለፓን አፍሪካ ባሕል ኅዳሴ፣ በሴቶች ተሳትፎና እኩልነት፣ በሰላምና ጸጥታ፣ በአፍርካ ነጻ ንግድ ቀጣና፣ በአየር ንብርት ለውጥ እና መሰል ጉዳዮች በርካታ ስራዎችን ማከናወን መቻሉን ገልጸዋል።
በአባል አገራቱ የሚደረጉ ያልተገቡ ውጫዊ ጣልቃ ገብነቶች ለመመከት ጥረት ተደርጓል ብለዋል።
በአባል አገራት መካከል የጋራ ልማት እንጂ ግጭቶች እንዳይኖሩ የተከናወኑ ተግባራትንም አንስተዋል።
ለአብነትም በታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ ጉዳይ በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ መካከል ሁሉም አሸናፊ የሚሆኑበት የሶስትዮሽ ድርድር እንዲያደርጉ ኅብረቱ ጥረት ስለማድረጉ መጥቀሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
አባል አገራቱ መቻቻል እና የጋራ ልማት እንደሚያስፈልግ የገለጹት ፕሬዝዳንት ሺሲኬዲ በአፍሪካ የሚደረግን ማንኛውም ኢ-ሕገ መንግሥታዊ የመንግሥት ለውጥ ሁላችንም ልናወግዘው ይገባል ብለዋል።
ከሕገ-መንግሥታዊ ድንጋጌ ውጭ የሚደረግ ማንኛውም የመንግሥት ለውጥ የኅብረቱ ድንጋጌ እንዲያወግዘው ገልጸው ዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ስርዓትን በአፍሪካ ማስፈን ይገባናል ሲሉም ጠይቀዋል።
በአየር ንብረት ለውጥ እና አገራትን በሚያስተሳስሩ ኢኮኖሚዊ ትብብሮች ላይም ይብልጥ መስራት ይገባል ነው ያሉት።
አገራቸው ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፤ ለአፍሪካ አንድነት እና ዕድገት በቁርጠኝነት ትሰራለች ሲሉም አረጋግጠዋል።
በአፍሪካ ኅብረት የሊቀመንበርንት ቆይታቸው ለተደረገላችው ትብብር አመስግነው፤ ለተተኪያቸው መልካም የሥራ ዘመን ተመኝተዋል።