ኢትዮጵያ የሰብአዊ ድጋፍ ለማዳረስ እያደረገች ያለቸውን ጥረት ዴንማርክ አደነቀች

ሚያዝያ 28/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያ የሰብአዊ ድጋፍ ለማዳረስ እያደረገች ያለቸውን ጥረት ዴንማርክ አደነቀች።
የገንዘብ ሚኒስትር የአህመድ ሽዴ ከዴንርክ የልማት ትብብር ሚኒስትር ፍሊሚንግ ሞለር ሞርቴንሰን ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱ የዴንማርክን የቆየ የኢትዮጵያ የልማት አጋር መሆኗን ያነሱት የገንዘብ ሚኒስትሩ በግጭት ወቅትም ሀገሪቱ ይህንን የልማት ድጋፏን በመቀጠሏ አመስግነዋል።
ሚኒስትሩ በግጭቱ የተጎዱ ክልሎችን ለመደገፍ መንግሥት እያከናወናቸው ያሉ የማገገሚያ እቅድና ግብአት የማሰባሰብ ሥራዎችን አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል።
የዴንማርክ የልማት ትብብር ሚኒስትር ፍሊሚንግ ሞለር ሞርቴንሰን በበኩላቸው ዴንማርክ ኢትዮጵያን ለመደገፍ ቅድሚያ እንደምትሰጥ ገልፀው ኢትዮጵያ ሰብአዊ ድጋፍ ለማዳረስ እያደረገች ያለቸውን ጥረት እንደሚያደንቁ ተናግረዋል፡፡
ሚኒስትሮቹ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የትብብር እንቅስቃሴ ለማስቀጠልና ለማጠናከር ያላቸውን ቁርጠኝነት ማረጋገጣቸውን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡