ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ኅብረት ዓመታዊ የፖለቲካ ምክክር አካሄዱ

ሚያዝያ 28/2014(ዋልታ) ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ኅብረት አመታዊ የፖለቲካ ውይይታቸውን ዛሬ በአዲስ አበባ አካሂደዋል።
በአውሮፓ ኅብረት እና በአፍሪካ፣ በካሪቢያን እና በፓሲፊክ ሀገራት መካከል በተደረሰው የኮቶኑ አጋርነት ስምምነት አንቀጽ 8 መሰረት ነው ውይይቱ የተካሄደው፡፡
ሁለቱ ወገኖች በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ግጭት እና የአውሮፓ ኅብረት እና የኢትዮጵያ ግንኙነትን በሚመለከት የተወሰዱ የሰብአዊ እና የተጠያቂነት እርምጃዎችን ጨምሮ የተለያዩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ከግምት ውስጥ በማስገባት የጋራ ተጠቃሚነትን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ መክረዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የኢትዮጵያ መንግሥት በሰሜን ያለውን ግጭት ለማስቆምና የሀገሪቱን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ እያከናወናቸው ያሉ የተለያዩ እርምጃዎችን ዳሰሳ አቅርበዋል።
የፍትህ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) በሰሜኑ ግጭት ወቅት በሁሉም አካላት የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን ጨምሮ መንግሥት የወሰደውን የተጠያቂነት እርምጃ በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ፤ የአማራና አፋርን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የድጋፍ መሰረቱን ማስፋትና ለዘላቂ ልማትና መልሶ ማቋቋም ሥራዎች ተገቢውን ትኩረት መስጠት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የአውሮፓ ኅብረት ተወካዮች መንግሥት የወሰደውን የሰላም ግንባታ ርምጃዎች እና በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል ያለውን የድንበር ግጭት እና በታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ የተካሄደውን የሶስትዮሽ ድርድር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የገባውን ቃል ማድነቃቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በመድረኩ ከሰብአዊ መብት ጥሰት እና ከተጠያቂነት እርምጃዎች በተጨማሪ በኢትዮጵያ ስላለው የንግድ ሁኔታ ከአውሮፓ ባለሃብቶች አንፃር የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት እና የዳበረ ኢኮኖሚ ለመገንባት ስለሚያስችለው ጉዳይ ተወያይተዋል።