የገርጂ ዘመናዊ መኖሪያ መንደር በተለያዩ አካላት ተጎበኘ

ግንቦት 7/2014 (ዋልታ) በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘው እና የአልሙኒየም ፎርምወርክ የግንባታ ቴክኖሎጂ ውጤት የሆነው የገርጂ ዘመናዊ የመኖሪያ መንደርን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጣሰው ወልደሃና (ፕ/ር) እና ባለሀብቱ ነጅብ አባቢያ ጎብኝተዋል፡፡
በጉብኝታቸውም ኮርፖሬሽኑ በግንባታ ቴክኖሎጂ እና አስተዳደር እያሳየ ባለው የላቀ አፈጻጸም የመኖሪያ መንደሩን በ18 ወራት ግንባታውን ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ መቃረቡ ተገልጿል።
ይህም በሀገሪቱ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ተስፋ ሰጪ መሆኑ ተነግሯል፡፡
በዚህ ፕሮጀክት ጥራትን፣ ቅልጥፍና እንዲሁም ዘመናዊነትን አጣምሮ እጅግ ዘመናዊ መኖሪያ መንደር በአጭር ጊዜ መገንባት መቻሉ ኮርፖሬሽኑ ብቃት ባላቸው እና የፕሮጀክት አስተዳደር እውቀት ባካበቱ አመራሮች እየተመራ መሆኑን ማሳያ መሆኑን የጉብኝቱ ተሳታፊዎች ገልፀዋል።
የመኖሪያ መንደሩ የተገነባበት እና የተመራበት አጠቃላይ ሂደቱ ለዘርፉ ምሁራን፣ አልሚ ባለሃብቶች እና ተማሪዎች በግንባታ እንዱስትሪው የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ለሚያደርጉት ሳይንሳዊ ጥረት ፍንጭ ሊሰጥ የሚችል ፕሮጀክት ሲሉም ነው የገለጹት፡፡
የመኖሪያ መንደሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ የውጭ አገራት ዜጎች እና በተለያዩ አካላት እየተጎበኝ ሲሆን በቀጣይ ከፕሮጀክቱ ልምድ ተወስዶ እንደሀገር በሰፋፊ የቤት ልማት ፕሮግራሞች ላይ ተግባራዊ ለማድረግ በሚቻልበት ሁኔታም ሰፊ ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝ የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመለክታል፡፡