ፐርፐዝ ብላክ አንድ ሚሊዮን ገበሬዎችን የአክሲዮን ባለቤት የማድረግ ዘመቻን አስጀመረ

ፐርፐዝ ብላክ

ግንቦት 30/2014 (ዋልታ) ፐርፐዝ ብላክ ኢቲ.ኤች አንድ ሚሊዮን ገበሬዎችን የአክሲዮን ባለቤት የማድረግ ዘመቻን አስጀምሯል።

ኩባንያው አርሶ አደሩን በምርት ሂደቱ ላይ በቴክኖሎጂ ከማገዝ ጀምሮ የገበያ እድል እስከ ማመቻቸት ድረስ አብሮ የሚሰራ ከመሆኑም ባሻገር አርሶ አደሮችን የፐርፐዝ ፕላንክ ኢቲ.ኤች ባለአክሲዮን በማድረግ በባለቤትነት እንዲያስተዳድሩት እድል የሚያመቻች መሆኑ ተገልጿል።

መርኃ ግብሩን በይፋ ያስጀመሩት የፐርፐዝ ብላክ ኢቲ.ኤች ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሰሀ እሸቱ (ዶ/ር) ከአርሲ ዞን በቆጂ ከተማ ለመጡ አርሶ አደሮች አቀባበል በማድረግ ኩባንያው በዓለም አቀፍ ደረጃ የጥቁሮችን ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ለመለወጥ ሲነሳ ያለ ግብርናና አርሶ አደሩ የሚታሰብ አለመሆኑን በማመን ጭምር መሆኑን አንስተዋል።

በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ሌሙና ቢልቢሎ ወረዳ አስተዳደር ሄርጳ ተሾመ በበኩላቸው መሬት ገፍቶ ሕዝብ እየመገበ ነገር ግን ዛሬም በድህነት ውስጥ ለሚገኘው ገበሬ ውለታው ተከፍሎ የሚያልቅ አለመሆኑን ገልፀው ኩባንያ አርሶ አደሩን ባለቤት ለማድረግ በዘመቻ መልክ እየሰራ ያለው ሥራ የሚበረታታ ነው ብለዋል።

በሁነቱ ላይ አቀባበል የተደረገላቸው የአርሲ ዞን አርሶ አደሮች አሁን ላይ ያለባቸውን ችግሮች ለመቅረፍ የሚታትር ተቆርቋሪ ኩባንያ በመኖሩ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል።

በታምራት ደለሊ

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW