የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ 195 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ አደረገ

ግንቦት 30/2014 (ዋልታ) የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ክትባትን ለዜጎች ለማዳረስና የጤና ዘርፉን ለማገዝ የ195 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ማድረጉን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የገንዘብ ድጋፋ ኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ክትባቶችን በሀገር አቀፍ ደረጃ ተደራሽ ለማድረግ የምታደርገውን ጥረት ለመደገፍና በግጭቶች የተጎዱ የሕዝብ ጤና ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም የሚረዳ ነው ተብሏል።

ወቅታዊው የገንዘብ ድጋፍ በጫና ውስጥ ላለው የኢትዮጵያ የጤና ሥርዓት አጋዥ ከመሆን በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት ከ30 በመቶ በታች ያለውን የኮቪድ-19 የክትባት ሽፋን ለማሳደግና በመላ ሀገሪቱ የክትባት ሥራዎችን በማስፋፋት የበሽታውን ስርጭትና ተጽዕኖ ለመቀነስ እንደሚረዳ በኢትዮጵያ የዓለም ባንክ ዳይሬክተር ኦስማን ዲዮን ተናግረዋል።

በእናቶች እና ህጻናት ጤና አጠባበቅ ረገድ፣ በሥነ-ምግብ እና ሌሎች ቁልፍ አገልግሎቶችን ተደራሽ ከማድረግ አኳያም የገንዘብ ድጋፉ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውና በግጭቱ የተጎዱ የገጠር አካባቢዎችን እና ተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለመድረስ ብሎም ለኢትዮጵያ የጤና ሥርዓት ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግ ታወቋል፡፡

በተጨማሪም ድጋፉ ኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ክትባት ግዢ ለማድረግ፣ የሆስፒታል የፅኑ ህሙማን ክፍል መሳሪያዎችን ለማሟላት፣ በኮቪድ-19 እና በሌሎች ህመሞች ላይ ያሉ ህመምተኞችን አያያዝ የበለጠ ለማሻሻል እንዲሁም የማኅበረሰብ ጤና ባለሙያዎችን ለማሰልጠን ይውላል መባሉን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

የገንዘብ ድጋፋ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2023 መጨረሻ ለ60 በመቶ ዜጎች የኮቪድ-19 ክትባትን ለማዳረስ የምታደርገውን ጥረት የሚያግዝ ሲሆን ይህ የ195 ሚሊየን ዶላር ተጨማሪ ድጋፍ የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ምላሽ የሰጠውን የገንዘብ ድጋፍ ከ495 ሚሊየን ዶላር ያደረሰው መሆኑ ታወቋል፡፡