በኦሮሚያ ልዩ ዞን ለአረንጓዴ አሻራ 25 ሺሕ ሄክታር መሬት መለየቱ ተገለፀ

ሰኔ 19/2014 (ዋልታ) በ4ኛው ዙር አረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ለ98 ሚሊየን ችግኝ ተከላ የሚውል 25 ሺሕ ሄክታር መሬት በጂ ፒ ኤስ በመለየት ዝግጅት ማጠናቀቁን የኦሮሚያ ልዩ ዞን አስታወቀ፡፡

በኦሮሚያ ክልል ፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ጫላ አደሬ እንዳሉት በዞኑ በሚገኙ 16 የመንግሥት ችግኝ ጣቢያዎች፣ በትምህርት ቤቶች፣ በሃይማኖት ተቋማትና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ወደ 98 ሚሊየን ችግኝ ለተከላ ተዘጋጅቷል፡፡

ለተከላ የሚውል 25 ሺሕ ሄክታር መሬት ተለይቶ ወደ 77 ሚሊየን የችግኝ ጉድጓድ መዘጋጀቱንም ገልጸዋል፡፡

ችግኞቹ ለከብቶች መኖ፣ ለምግብና ለደን ሽፋን የሚውሉ መሆናቸውን የገለፁት ኃላፊው በዚህ ዓመትም ሀገር በቀል የሆኑና ለምግብነት በሚውሉ ችግኞች ላይ ትኩረት መደረጉን ተናግረዋል፡፡

በዚህም በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ለተከላ ከተዘጋጁት 98 ሚሊየን ችግኞች መካከል 11 ሚሊየን የሚሆኑት ለምግብነት የሚውሉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በዞኑ ባለፈው ዓመት ከተተከሉ ችግኞች ውስጥ 86 በመቶ የሚሆኑት መፅደቃቸውንም ተናግረዋል፡፡

በደረሰ አማረ