ቤንዚን ከባዕድ ነገር ጋር ቀላቅሎ ሲሸጥ የነበረ ማደያ ታሸገ

ሰኔ 19/2014 (ዋልታ) በጌዴኦ ዞን በወናጎ ከተማ ከ85 ሺሕ ሊትር በላይ ቤንዚን ከባዕድ ነገር ጋር ቀላቅሎ ለኅብረተሰቡ ሲሸጥ የነበረ ኦይል ሊቢያ ማደያ ማሸጉን የዞኑ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ አስታውቋል።

የጌዴኦ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ ምስጋና በራሶ መንግሥት የሕዝብን ፍላጎት ለማሟላት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት የነዳጅ አቅርቦት ለማኅበረሰቡ ተደራሽ እንዲሆን በትኩረት እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።

ከወናጎ ከተማ አስተዳደር ጋር በቅንጅት ከሕዝቡ በደረሰ ጥቆማ መሠረት ከባዕድ ነገር ጋር ተቀላቅሎ ሲሸጥ የነበረ ነዳጅ ለማጣራት በተደረገ ክትትል ቤንዚኑ የጥራት ጉድለት እንዳለበት ከኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ለማረጋገጥ መቻሉን ተናግረዋል።

የወናጎ ከተማ ምክትል ከንቲባና የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ ስንታየሁ ጎሎ በበኩላቸው በከተማዋ እየተበራከተ የመጣውን ህገወጥ የንግድ እንቅስቃሴና ከደረጃዎች በታች የሚመጡ ምርቶችን የመቆጣጠር ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።

በዚህም መሠረት ከ85 ሺሕ ሊትር በላይ ቤንዚን ከባዕድ ነገር ጋር ቀላቅሎ ለኅብረተሰቡ ሲሸጥ የነበረ በኦይል ሊቢያ ማደያ ላይ ጥልቅ ክትትል በማድረግ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱን አመላክተዋል።

ህገ-ወጥ ተግባራትንና መሰል ችግሮች ለመቅረፍ ከተማ አስተዳደሩ ከዞኑ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ጋር በጋራ በመሆን የክትትል ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል መባሉን የዞኑ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ የላከልን መረጃ አመላክቷል፡፡