የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በ120 ሰራተኞች ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ

ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሽፈራው ተሊላ

ነሐሴ 12/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት 221 አመራር እና ሰራተኞች ላይ ማጣራት አካሂዶ 120 ሰራተኞች ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ።

አገልግሎቱ ከደንበኞች እና ባለድርሻ አካላት በቀረበለት 145 ጥቆማዎች መሰረት በ221 አመራር እና ሰራተኞቹ ላይ ምርመራ እና ማጣራት ሲያካሄድ ቆይቶ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባልተወጡ 120 ሰራተኞች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰዱን ነው ያስታወቀው፡፡

ቀሪ 101 የሚሆኑ ሰራተኞች ጉዳያቸው በተቋሙ የዲሲፕሊን ኮሚቴ እየታየ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሽፈራው ተሊላ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

በአጠቃላይ በ2014 በጀት ዓመት ከደንበኞች የመጣውን ቅሬታ ጨምሮ ተቋሙ ያስቀመጠውን የውስጥ አሰራር ያላከበሩ እና የሥነ – ምግባር ጥሰት በፈጸሙ 1 ሺሕ 50 አመራር እና ሰራተኞች ላይ የተለያዩ አስተዳደራዊ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል በአዲስ አበባ አንዳንድ አካባቢዎች ያጋጠመው የኃይል መቆራረጥ ሰበታ ላይ ትልቅ ትራንስፎርመር በመቃጠሉ ምክንያት እንደሆነ የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው በሚቀጥሉት ጊዜያት ችግሩን በመፍታት እያገጠመ ያለውን የኃይል መቆራረጥ ችግር ለመፍታት እየተሰራ ነው ብለዋል::

ከመብራት ቆጣሪ ጋር በተያያዘ ከተጠቀሙት በላይ የገንዘብ መጠን እየመጣባቸው ያሉ ደንበኞች ተቋሙ አስፈላጊውን ማጣራት እያደረገ እንደሚገኝ እና ወደፊት መፍትሄ እንደሚያገኝ አመላክተዋል::

ተቋሙ የ2014 በጀት ዓመት አፈፃፀም እና የ2015 በጀት ዓመት እቅድ እንዲሁም በአጠቃላይ አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ላይ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥቷል።

በሜሮን መስፍን