ነሐሴ 17/2014 (ዋልታ) በመጪው ዓመት ለሚካሄደው ሀገራዊ ምክክር የሲቪል ማኅበራት እና የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚጠበቅባቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል ተባለ።
የሲቪል ማኅበራት እና የፖለቲካ ፓርቲዎች በመጪው ዓመት ለሚካሄደው ሀገራዊ ምክክር ውጤታማነት ሚናቸው ምን መሆን አለበት? በሚል ሀሳብ ውይይት እየተካሄደ ነው።
በውይይቱም የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን አመራሮች፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ አለሙ ስሜን (ዶ/ር) ጨምሮ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ የሲቪል ማኅበራት አመራሮች፣ አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር ሄኖክ መለሰ ሀገራዊ ምክክሩ የሀገር ኅልውና እንዲጠበቅ ሕዝቦች በተረጋጋና በሰላማዊ መንገድ እንዲኖሩ እንደሚያስችል ተናግረዋል።
እንደ ሀገር ከዚህ ቀደም ያልተስማማንባቸውን ጉዳዮች በመፍታት በአብሮነት ለመሻገር ምክክሩ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ገልፀው ለተግባራዊነቱ የድርሻውን እንደሚወጡም ተናግረዋል፡
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ራሄል ባፌ (ዶ/ር) ሀገር የተረጋጋች እንድትሆንና ሰላማዊ መንገድን የተከተለ የዲሞክራሲ ሥርዓት ለመገንባት ሀገራዊ ምክክሩ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሚካሄደው ብሔራዊ ምክክር ከሌላው ዜጋ በተለየ መንገድ ለተግባራዊነቱ መስራት እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።
በሳራ ስዩም
ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW