በአሜሪካ በአንድ ምሽት ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል ከ70 ሺሕ ዶላር በላይ ተሰበሰበ

አምባሳደር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር)

ነሐሴ 17/2014 (ዋልታ) በአሜሪካ ዋሸንግተን ዲሲ በአንድ ምሽት በተካሄደ የገቢ ማሰባሰቢያ መርኃ ግብር ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሚውል ከ70 ሺሕ ዶላር በላይ ተሰበሰበ።

ለሕዳሴ ግድብ ድጋፍ ማሰባሰቢያ በተዘጋጀው “ማይ ገርድ ዶት ኮም” (www.mygerd.com) ድረ-ገጽ የተሰበሰበው 310 ሺሕ ዶላርም ለመንግሥት ገቢ ተደርጓል።

“ደርሰናል እናጠናቅቀዋለን” በሚል መሪ ሀሳብ በዋሺንግተን ዲሲ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተዘጋጀው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የገቢ ማሰባሰቢያና የምስጋና መርኃግብር በአካልና በበይነ መረብ በማቀላቀል (ሀይብሪድ) ተካሂዷል።

በዚህ ወቅት በአሜሪካ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን ለሕዳሴ ግድብ በገንዘብ፣ በእውቀት፣ በውግንና (አድቮኬሲ)፣ በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ቅስቀሳ፣ በምርምርና በተለያዩ መስኮች እያደረጉት ያለውን ድጋፍ አድንቀዋል።

“የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የአንድነታችን ድንቅ ማሳያና ለልማት ያለንን ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥ ነው” ያሉት አምባሳደሩ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን የሦስተኛውን ዙር የግድቡ የውሃ ሙሌት በመጠናቀቁና ሁለተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት በመጀመሩ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።

ሁሉም አካል የሕዳሴ ግድብ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድጋፍ ማድረጉን መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል።

በተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ በበኩላቸው የሕዳሴ ግድብን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ የኢትዮጵያን የለውጥና እድገት ሕልሞች እውን ለማሳካት ልናውለው ይገባል ብለዋል።
የገቢ ማሰባሰቢያና የምስጋና መርኃግብር ተሳታፊዎች ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በሁሉም መስኮች ድጋፋቸውን ማድረግ እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
በመርኃግብሩ ላይ በአካልና በይነ መረብ ከ200 በላይ ሰዎች መሳተፋቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ አመላክቷል።
ለሕዳሴ ግድብ ድጋፍ ማሰባሰቢያ በተዘጋጀው “ማይ ገርድ ዶት ኮም” ( www.mygerd.com) ድረ-ገጽ የተሰበሰበው 310 ሺሕ ዶላር ለመንግሥት ገቢ የተደረገ ሲሆን ሐምሌ 13 2013 ዓ.ም ይፋ የተደረገ የበይነ መረብ አማራጭ ሲሆን ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን ለሕዳሴ ግድቡ ድጋፍ የሚያደርጉበት ነው።
ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በድረ-ገጹ 313 ሺሕ 771 ገቢ ለግድቡ ተሰብስቧል።