የቲቢ ላቦራቶሪ ምርመራን ሀገር አቀፍ የመረጃ ትስስር ማጠናከር የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

ዶ/ር ሊያ ታደሰ

ነሐሴ 23/2014 (ዋልታ) ሪች ኢትዮጵያ ከጤና ሚኒስቴርና ከኢትዮጵያ የኅብረሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ጋር በመተባበር የተቀናጀ የቲቢ ላቦራቶሪ ሥርዓት ከበይነ መረብ ጋር የማስተሳሰር ፕሮግራም በሀገር አቀፍ ደረጃ አስጀመሩ።

ፕሮጀክቱን ያስጀመሩት የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ የተቀናጀ የላቦራቶሪ ሥርዓት ውጤታማ እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን ገልጸው ቲቢን ለማጥፋት እንደ ሀገር ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

በሀገሪቱ ባሉ 324 የህክምና ተቋማት የሚገኙ 374 የጂንኤክስፐርት ላቦራቶሪ ማሽኖች በ2 ሰዓት ውስጥ የቲብ ምርመራ ውጤት ለታካሚዎች እያደረሱ እንደሆነም ተናግረዋል።

በዓለም ላይ የቲቢ በሽታ ጫና ካለባቸው 30 ሀገራት ኢትዮጵያ አንዷ ናት ያሉት ሚኒስትሯ ይህን ለመከላከልና ለመቆጣጠር 4 ሺሕ በሚደርሱ የጤና ተቋማት ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ነው የተናገሩት።

አሁን ካሉት 374 ጂንኤክስፐርት የመርመሪያ ማሽኖች በተጨማሪ በዩኤስ አይድ የገንዘብ ድጋፍ 126 የቲቢ መመርመሪያ ማሽን ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ መደረጉም ተገልጿል፡፡ ማሽኖቹ ቲቢን ከመመርመር ባለፈ የፀረ ቲቢ መድኃኒት የተላመደ ቲቢ መመርመር ያስችላሉም ተብሏል።

ዛሬ ይፋ የሆነው የተቀናጀ የቲቢ መመርመሪያ ሥርዓት የጂንኤክስፐርት ቲቢ መመርመሪያ መሽኖችን በሶፍት ዌር ከበይነ መረብ ጋር በማገናኘት ከማሽኖቹ የሚወጣው መረጃ ያለምንም የጊዜ ቆይታ በፍጥነት የሚያዳርስ እንደሆነም ተነግሯል።