ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አልጀርስ የሚገኘውን የሰማዕታት መታሰቢያ ሙዚየም ጎበኙ

ነሐሴ 23/2014 (ዋልታ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአልጀሪያ እያደረጉት ባለው ይፋዊ የሥራ ጉብኝት በአልጀርስ የሚገኘውን የሰማዕታት መታሰቢያ ሙዚየም ጎብኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስፍራው የአበባ ጉንጉንም አኑረዋል።

በአልጀርስ የሚገኘው የሰማዕታት መታሰቢያ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1982 አልጀሪያ 20ኛ ዓመት የነጻነት በዓሏን ስታከብር ለአገሪቷ ነጻነት የህይወት መሰዋዕትነት የከፈሉ ዜጎችን ለማሰብ ነው በይፋ ተመርቆ ለጎብኝዎች ክፍት የሆነው።

የሰማዕታት መታሰቢያው በውስጡ 302 ጫማ ርዝመት ያለው ሐውልትና አልጀሪያዊያን ለአገራቸው ነጻነት የከፈሉትን ዋጋ የሚያሳይ ሙዚየም ይዟል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በትናነትናው እለት ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት አልጀሪያ መግባታቸው የሚታወስ ሲሆን በቆይታቸውም ከአልጀሪያ ፕሬዝዳንት አብዱል መጅድ ታቡኔ ጋር በመገናኘት የሁለቱ አገራት ግንኙነት በሚጠናከርባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ኢትዮጵያና አልጀሪያ ረጅም ዘመናት ያስቆጠረ ወዳጅነት ቢኖራቸውም ግንኙነታቸውን በኢኮኖሚ በማስተሳሰር ረገድ የሚጠበቅባቸውን ያህል እንዳልሰሩ መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የሁለቱ አገራት ግንኙነት ይበልጥ እየተጠናከረ የመጣ ሲሆን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጉብኝትም የዚሁ ማሳያ ነው ተብሏል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW