ትምህርት ቤቶች ከእውቀት መገብያነት ባሻገር የሰላም እሴት የሚጎለብትባቸው ማዕከላት ሊሆኑ ይገባል ተባለ

የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዷለም

መስከረም 4/2014 (ዋልታ) ትምህርት ቤቶች ከእውቀት መገብያነት ባሻገር የሰላም እሴት የሚጎለብትባቸው ማዕከላት ሊሆኑ እንደሚገባ የሰላም ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ፡፡

የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዷለም የዜጎችን የኑሮ ሁኔታና ህይወት ማሻሻል የሚቻለው በቅድሚያ አስተማማኝ ሰላም ሲረጋገጥ መሆኑን ገልጸው ችግሮችን በሰላምና በውይይት የመፍታት ባህል ሊዳብር ይገባል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ብዝሃ-ማንነት ያላቸው ዜጎች የሚኖሩባት ሀገር እንደመሆኗ መጠን ልዩነቶችን በሰለጠነ መንገድ የመፍታት ባህል ማደግ እንዳለበትም ነው የተናገሩት።

ከዚህ አኳያ የሰላም ሚኒስቴር ልዩነቶች በውይይት የመፍታት ባህል እንዲጎለበት የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ ስለመሆኑ ገልጸዋል።

ከታች ከትምህርት ቤት ጀምሮ የሰላም ግንባታን በትምህርት ሥርዓቱ በማካተት ጭምር ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህል እንዲዳብር ይሰራል ያሉት ሚኒስትሩ በትምህርት ቤቶች የሰላም ክበባት እንዲጠናከሩ እንደሚደረጉም አመልክተዋል፡፡

ግጭቶች ከመከሰታቸው አስቀድሞ ለመካላከል የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው፣ በዚህ ረገድ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት የሚያስችሉ ህዝባዊ መድረኮችን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡

ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት የሚያስችሉ ህዝባዊ መድረኮች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ነው የተናገሩት፡፡

ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም እንዲሁ፡፡

ችግሮችን በውይይት በመፍታት ዘላቂ ሰላም ለመገንባት ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ሚና መወጣት እንዳለበትም ሚኒስትሩ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡