ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሩ ለመስቀል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

መስከረም 16/2015 (ዋልታ) የኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ፣ ሀረሪ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች፣ የጋምቤላ ክልሎች እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለደመራና መስቀል በዓላት የእንኳን አደረሳችሁ መልካም ምኞት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ክረምት አልፎ በጋ ሲተካ፣ አበቦች በምድር ላይ ፈክተው መዓዛቸውን ሲሰጡ፣ በደመና ተሸፍና የነበረች ፀሓይ ብርሐኗን ፈንጥቃ፣ ክረምቱ ለፀደይ ወራት ስፍራውን በሚለቅበት በዚህ ወቅት እንኳን ለታላቁ የመስቀል በዓል በሠላም አደረሳችሁ ለማለት እወዳለሁ ብለዋል፡፡

የመስቀል በዓል በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ በፍቅርና በአንድነት የሚከበር በዓል ከመሆኑም ባሻገር ያለው ለሌለው የሚለግስበት፣ የፍሰሃና የደስታ፣ መተሳሰብና አብሮነት የሚወደስበት ታላቅ በዓል ነው ሲሉም አክለዋል፡፡

በ2014 ዓ.ም ያጋጠሙንን በርካታ ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር ሕዝባችን ወደ ቀደምት ባሕሉ እንዲመለስ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥርዓቶችን በአዋጅ በማስፀደቅ በባሕላዊ መንገድ የዳበሩ አስተሳሰቦች የጋራ ልማትን በዜግነት አገልግሎት፣ ፍትህን ተደራሽ ለማድረግ ባሕላዊ ፍ/ቤቶችን በማስፋፋት፣ የጋራ ሰላምን በጋቻና ስርና አደረጃጀት ማረጋገጥ እንዲሁም ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችን በቡሳ ጎኖፋ ሥርዓት ለመቋቋም እየተሠራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ለመስቀል በዓል ባስተላለፉት የአንኳን አደረሳችሁ መልዕክት የመስቀል በዓል፣ በክፉዎች ምኞትና ጥረት የሚያልቅና የሚያበቃ ነገር እንደሌለ የተማርንበት ነው ብለዋል፡፡

መስቀሉን ሰውረው የቀበሩት ሰዎች፣ የመስቀሉ ነገር በእነርሱ አሸናፊነት ያለቀ፣ የተጠናቀቀ መስሏቸው ነበር፤ ታሪክ ሠሪ ሰውና ታሪካዊ ጊዜ እስኪመጣ ድረስ እውነትም ያለቀ መስሎ ነበር ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ንግሥት ዕሌኒ የምትባል ታሪክ ሠሪና ነገሮች የተለወጡበት ታሪካዊ ጊዜ መጣ፤ መስቀሉም ከተቀበረበት ወጣ፤ ታሪክም ተለወጠ ሲሉ አክለዋል።

የክፉዎች ታሪክ እየተለወጠ ነው፤ ታሪክ እናድርጋት ያሏት ኢትዮጵያ ታሪክ እያደረገቻቸው ነው፤ የኢትዮጵያ ጉዞ በክፉዎች ድል አድራጊነት ሊጠናቀቅ እንደማይችል እየታየ ነው፤ ታሪክ ሠሪ ጀግኖችና ታሪካዊ ጊዜ ገጥሟል፤ የኢትዮጵያውያን የአንድነትና የአሸናፊነት መንፈስ ከተቀበረበት ወጥቷል፤ ከእንግዲህ እንደ ችቦ እያበራ ይቀጥላል እንጂ ማን ያቆመዋል ሲሉም በመልዕክታቸው አመልክተዋል፡፡

የሀረሪ ክልል መንግስት በበኩሉ ለመላው የሀገራችን እና የክልሉ የክርስትና እምነት ተከታዮች በየዓመቱ በድምቀት ለሚከበሩት የደመራና የመስቀል በዓል በሰላም አደረሳችሁ የሚል መልዕክቱን አስተላልፏል።

የመስቀል በዓል ለረጅም ጊዜ የተራራቁ የቤተሰብ አባላት እና ወዳጅ ዘመዳሞች የሚገናኙበት፣ የተጣሉ የሚታረቁበት፣ የተቸገሩ ወገኖች የሚደገፉበት፣ አዲስ ጎጆ የሚመሰረትበት እና ሌሎች ማህበራዊ ኩነቶች የሚከወኑበት ታላቅ በዓልም ጭምር ነውም ብሏል በመግለጫው፡፡

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ማስረሻ በላቸው ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት የመስቀል በዓል ከሃይማኖታዊ አስተምህሮቱ እና ከመንፈሳዊ እውነትነቱም ባሻገር የሚያስተምረን እና በውል እንድናስተውል የሚያስገድደን እውነት የቱንም ያህል ዘመን፣ በምንም ያህል ውሸትና ቅጥፈት፣ ተንኮልና ሤራ፣ በየትኛውም ስልጣን እና ክፋት ቢትሸፈንም በዘላቂነት ግን ልትቀበር እንደማትችል አይነተኛ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

እኛ በዓላማ ከጸናን፣ ካልተከፋፈልን ለሐሰተኞች ጆሮና ልቦናችንን ከነፈግን እውነት ብትቀበር እንኳን እንደ ታላቁ መስቀል ሁሉ ቢዘገይም አንድ ቀን ግን ነፃ ታወጣናለች ሲሉም አክለዋል፡፡

የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እርስቱ ይርዳ በበኩላቸው የመስቀል በዓል ሃይማኖታዊ በዓል ቢሆንም ኢትዮጵያዊያን ይህን በዓል የባህላቸው፣ የትውፊታቸው፣ የማኅበራዊ ዕሴቶቻቸው አካል አድርገው ነው የሚያከብሩት ብለዋል፡፡

የመስቀል በዓል አከባበር ልዩ የሚያደርገው እና የዓለምን ትኩረት ሊስብ የቻለውም ከሃይማኖታዊ ፋይዳው ባሻገር ባህላዊ ክዋኔው በጣምራ በመከበሩ መሆኑን የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ በሁሉም አካባቢዎች መስቀል የሰላም፣ የአብሮነት፣ የመተሳሰብ፣ የመደጋገፍ፣ የመከባበር እንዲሁም የተጣሉ/የተኮራረፉ ይቅር የሚባባሉበት እሴታችን ደምቆ የሚታይበት በዓል ነው ብለዋል፡፡

በክልላችን በአንዳንድ ብሔሮችና ብሔረሰቦች የመስቀል በዓልን የዘመን መለወጫ በዓል ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከመስከረም 12 ጀምሮ በዓሉን በልዩ ልዩ ኩነቶች በማክበር የተለየ ስሜት እንዲፈጠር ይደረጋል፡፡ ይህም ነው መስቀልን ተናፋቂ በዓል እንዲሆን ያደረገው ሲሉም አክለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ከንቲባዋ በመልዕክታቸው መስቀል ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ሁሉ ያለዘር፣ ያለቀለም፣ ያለፆታ፣ ያለሀይማኖትና ያለልዩነት መውደዱን ህይወቱን በመስጠት ወደር የማይገኝለትን ፍቅርን የገለፀበት በዓል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

መስቀል ድንቅ ሃይማኖታዊ ሥርዓት፣ እሴትና ታይቶ የማይጠገብ ትውፊታዊ ይዘትና ተፈጥሯዊ መስህብ ገፅታዎች የተላበሰ የሀገር መገለጫና ኩራት ከሆኑ በዓላት አንዱ መሆኑንም አመልክተዋል።

መስቀል የፍቅር፣ የሰላምና የአብሮነት በዓል እንደሆነና የመስቀል ደመራ በዓል የጨለማው በብርሃን መሸነፍ ማሳያ መሆኑን ገልጸው ይህንን በዓል በፍቅር፣ እርስበእርስ በመተሳሰብ ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ በመስራት፣ ጀግኖችን በማክበር፣ ደጀንነትን የበለጠ በማረጋገጥ፣ አንድነትን በማጽናት እንደ ደመራው ደምቀን ጨለማ በሆነብን ሁሉ ላይ እያበራን በአሸናፊነት እንቀጥል ሲሉም መልዕክተ አስተላልፈዋል።

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ ለመስቀል በዓል ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ህዝበ ክርስቲያኑ የመስቀል በዓልን ሲያከብር እሴቱን በጠበቀ መልኩ የተቸገሩ ወገኖችን በማብላትና የተጠሙትን በማጠጣት ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ህብረተሰቡ የተለመደ የመተዛዘንና የመረዳዳት ባህሉንም በመተግበር በዓሉን ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር እንዲያከብርም ጥሪ አቅርበዋል።

የተጀመረው የእድገት እና የብልጽግና ጉዞ እውን እንዲሆን በየአካባቢያችን ሰላማችንን አጽንተን ያሉንን ጸጋዎች በመጠቀም ሙሉ አቅማችንን እና ትኩረታችንን በልማት ላይ ልናደርግ ይገባል ብለዋል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured
ቲዊተር https://twitter.com/walta_info
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!