በኤሌክትሪክ ኃይል ላይ ያተኮረ ትራንስፖርትን ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው ተባለ

ዳግማዊት ሞገስ

መስከረም 16/2015 (ዋልታ) በኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት በኤሌክትሪክ ኃይል ላይ ያተኮረ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዳግማዊት ሞገስ ገለፁ።

በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት “በኤሌክትሪክ ላይ የተመሰረተና ጤናማ ትራንስፖርትን ማበረታታት” በሚል መሪ ሃሳብ ምክክር እየተካሄደ ነው።

ሚኒስትሯ ዳግማዊት ሞገስ በምክክር መድረኩ ላይ እንደገለፁት በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በዓለም ላይ ከፍተኛ የድርቅ፣ የጎርፍ መጥለቅለቅና ሌሎች ችግሮች እየተፈጠሩ ይገኛሉ።

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፉ በነዳጅ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ የአየር ንብረት ለውጥ ከሚከሰትባቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ ነው ብለዋል።

በቀጣይ 10 ዓመት በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችንና የህዝብ ትራንስፖርቶች ወደ አገልግሎት ለማስገባት የማበረታቻ ሥርዓት መዘርጋቱን ተናግረዋል፡፡

የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲም በኤሌክትሪክ የሚሰራ የትራንስፖርት አገልግሎትን ለማስፋት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ካሪኩለም ቀርፆ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ በመሆኑ ተገቢው ድጋፍ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፍሬው ተገኘ (ዶ/ር) በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የሀገሪቱ ኢኮኖሚ የሚፈልገውን የሰለጠነና የበቃ የሰው ኃይል ለማቅረብ በጥናት ላይ ተመስርቶ እየሰራ ነው ብለዋል።

በመድረኩ ላይ አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴን ጨምሮ ሌሎች የኤሌክትሪክ መኪኖች የሚገጣጥሙ ድርጅቶች ያላቸው ባለሃብቶች፣ ምሁራንና የፌዴራል የስራ ኃላፊዎች መሳተፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡