የክልሉ 1ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ነው

ኅዳር 17/2015 (ዋልታ) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል መንግሥት 1ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር እና ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች በምስረታ በዓሉ ላይ ተገኝተዋል፡፡

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ክልሉ እንዲቋቋም ትግል ላደረጉ አካላት እና ለመላው የክልሉ ህዝቦች የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ክልሉ የህብረ ብሔራዊ ማንነት የሚንፀባርቅበት መሆኑን የጠቀሱት አፈ ጉባኤው ክልሉ ልክ እንደ ነባር ክልል በሀገራዊ ጉዳይ ላይ በሚገባ የራሱን አሻራ ማኖር የቻለ እና ጠንካራ አመራር ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይም ክልሉ የጀመረውን የልማት ስራ በማጠናከር የኢትዮጵያን ብልፅግና እውን ለማድረግ መትጋት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በበኩላቸው ክልሉ እምቅ የተፈጥሮ ሀብት እና ማዕድን ባለቤት መሆኑን ጠቅሰው ከተመሰረተ አጭር ጊዜ ቢሆንም በርካታ መሰረተ ልማቶች እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መገንባታቸውን ገልጸዋል፡፡

በክልሉ ያለው የግብርና ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ያነሱት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ይሁን እንጂ ክልሉ ከፍተኛ የበጀት እጥረት እንዳለበት ገልጸው መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ለክልሉ ሊያደርግ እንደሚገባ ጠይቀዋል።

ባለፉት ጊዜያት በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ይስተዋል የነበረው የፀጥታ ችግር በተሰራው ጠንካራ የክትትል ስራ ግጭቶችን መቆጣጠር መቻሉን ገልጸው የተገኘውን አንፃራዊ ሰላም አጠናክሮ ለማስቀጠል ተከታታይነት ያለው ስራ ሊሰራ ይገባልም ነው ያሉት፡፡

ሜሮን መስፍን (ከቦንጋ)