ታኅሣሥ 17/2015 (ዋልታ) የጉምሩክ ኮሚሽን እና ገቢዎች ሚኒስቴር ለወሎ ዩኒቨርሲቲ 50 ላፕቶፕ ኮምፒውተሮችንና አምስት የተለያዩ ተሽከርካሪዎችን ድጋፍ አደረጉ።
ድጋፉን የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴና የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ ለዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት መንገሻ አየለ (ዶ/ር ) በደሴ ከተማ አስረክበዋል።
በድጋፍ ርክክቡ ላይ የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ ዩኒቨርሲቲው ለገጠሙት ችግሮች እጅ ሳይሰጥ ችግርን ወደ ዕድል በመቀየር በአፋጣኝ ወደ መማር ማስተማር ስራው መግባቱን አድንቀዋል።
የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ በበኩላቸው ኮሚሽኑ ከዩኒቨርሲቲው ጋር ያለው ግንኙነት በመስጠትና በመቀበል ላይ ብቻ ያተኮረ ሳይሆን በቀጣይ አንኳር በሆኑ ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ላይ ከዩኒቨርሲቲው ጋር ለመስራት የሚያስችል የሁለትዮሽ ስምምነት እንደሚደረግ ጠቁመዋል።
የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት መንገሻ አየለ (ዶ/ር) በርክክቡ ወቅት ዩኒቨርሰቲው በጦርነቱ ምክንያት 12 ቢሊዮን ብር የሚገመት የንብረት ውድመት እንደደረሰበት ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው በአጭር ጊዜ ተደራጅቶ ወደ ሥራ እንዲገባ የሁለቱ ተቋማት ሚና ከፍተኛ መሆኑን ፕሬዝዳንቱ ጠቅሰው ስለተደረገው ድጋፍ ማመስገናቸውን ከአማራ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡