በቦረና በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ አሰባስበው ያስረከቡ አካላት እንዲመዘገቡ ጥሪ ቀረበ

መጋቢት 3/2015 (ዋልታ) የኦሮሚያ ክልል መንግስት በቦረና በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ አሰባስበው ያስረከቡ እና በማሰባሰብ ላይ ያሉ አካላት አስፈላጊውን ሰነድ በመያዝ እንዲመዘገቡ ጥሪ አቀረበ፡፡

ክልሉ ጉዳዩን አስመልክቶ ባስተላለፈው መልዕክት በአንዳንድ ዞኖች በድርቅ ምክንያት በሰውና በእንስሳት ላይ ያጋጠመውን የምግብና የውሃ እጥረት በጋራ ለመፍታት እንዲቻል የድጋፍ ጥሪ መደረጉን አንስቷል፡፡

ይህን ተከትሎም ግለሰቦች፣ የግል ድርጅቶች፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እንዲሁም መላው ህብረተሰብ አስደናቂ በሆነ መልኩ ምላሽ በመስጠቱ ክልሉ የመጀመሪያው ዙር እውቅና ሰጥቷል፡፡

አሁንም በክልሉ በድርቁ ለተጋለጡ ወገኖች በቡድንም ሆነ በተናጠል ድጋፍ የሰበሰቡም ሆነ እየሰበሰቡ የሚገኙ አካላት ገንዘቡን ለዚሁ ዓላማ ተብለው በቡሳ ጎኖፋ ኦሮሚያ ተከፍተው ይፋ በተደረጉ የሒሳብ ቁጥሮች ያስገቡበትን የባንክ ስሊፕ እንዲሁም በዓይነት ድጋፍ ያደረጉበትን ሰነድ በመያዝ እንዲመዘገቡ ጥሪ አቅርቧል፡፡

ምዝገባው ሳሪስ አዲስ ጎማ ፋብሪካ ፊት ለፊት በሚገኘው የቡሳ ጎኖፋ ኦሮሚያ ዋና መስሪያ ቤት ከመጋቢት 4 እስከ 5 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ እንደሚካሄድ ተገልጿል።

በዚሁ መሠረት የተመዘገቡ አካላት መጋቢት 6 ቀን 2015 ዓ.ም ከጧቱ 4፡00 ሰዓት ጀምሮ በኦሮሚያ ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት በሚደረገው 2ኛ ዙር የርክክብና የእውቅናና ሥነ ሥርዓት ላይ እንዲገኙ ጥሪ መቅረቡን የኦሮሚያ ክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡