ሚኒስቴሩ ከዘንድሮ የበጋ መስኖ ስንዴ ከ52 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ አስታወቀ

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)

መጋቢት 3/2015 (ዋልታ) በዘንድሮ ዓመት ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ መሸፈኑንና ከ52 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የሚኒስቴሩ አመራሮች፣ የክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች እየለማ ያለውን የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ጎብኝተዋል፡፡

በጉብኝቱ ወቅት የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ጉብኝቱ አንዱ ክልል ከሌላው የተሻሉ ልምዶችን የሚቀስምበት፣ ተመራማሪዎችና የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ምክራቸውን የሚለግሱበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዘንድሮ ዓመት ከበጋ መስኖ ስንዴ ከ52 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ የገለጹት ሚኒስትሩ ምርቱ ተሰብስቦ ወደ ገበያ ሲገባ እንደ ሀገር በአሁኑ ወቅት እየታየ ያለውን የገበያ አለመረጋጋት በከፍተኛ ደርጃ ይቀርፋል እንደሚቀርፍ ተናግረዋል፡፡

በአርሶ አደሩ አካባቢ ከስንዴ ዋጋ ተመን ጋር ተያይዞ የሚነሳውን ቅሬታን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ አርሶ አደሩ ከዚህ ዋጋ በላይ አትሸጥም ተብሎ የተቀመጠ አቅጣጫ የለም፤ ነገር ግን አርሶ አደሮች አምርተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ የመነሻ ዋጋ ተመን ብቻ መወሰኑን ገልጸዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል የግብርና ቢሮ ኃላፊ ጌቱ ገመቹ በበጋ መስኖ ስንዴ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት እንደተቻለ ገልጸው በዘንድሮ ዓመት እንደ ክልል ከ1.1 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ በመሸፈን ከ38.5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት እየተሰራ መሆኑን መናገራቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡