በከተማ አስተዳደሩ ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ ባለፉት 8 ወራት ከ402 ሚሊየን በላይ ብር ተሰበሰበ

መጋቢት 3/2015 (ዋልታ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለፉት ስምንት ወራት ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከ402 ሚሊየን በላይ ብር መሰብሰቡን የአስተዳደሩ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ገለጸ።

የጽህፈት ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ምስክር ነጋሽ እንደገለጹት ባለፉት ስምንት ወራት በስጦታና በቦንድ ግዥ ከ402 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰብስቧል።

በድጋፉ የከተማው ሕዝብ፣ ባለሃብቶችና ተቋማት ተሳትፎ ማድረጋቸውን ጠቁመው በቀጣይም ለግድቡ ግንባታ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

ጽህፈት ቤቱ የተለያዩ የድጋፍ ማሰባሰቢያ መርኃ ግብሮችን በማዘጋጀት በስጦታና በቦንድ ሽያጭ የሚሰበስበውን ድጋፍ ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የግድቡ ሥራ ከጀመረበት ጀምሮ እስካሁን ድረስ በከተማ አስተዳደሩ ደረጃ 4 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር መሰብሰቡን ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ አመላክቷል።