ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በቦንጋ ከተማ በአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች እየተሰራ ያለው ስራ ተስፋ ሰጪ መሆኑን ገለጹ

መጋቢት 3/2015 (ዋልታ) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በቦንጋ ከተማ በአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች እየተሰራ ያለው ስራ ተስፋ ሰጪ መሆኑን ገለጹ፡፡

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ከፌዴራልና ክልል ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመሆን በቦንጋ ከተማ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የስራ እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል።

በቦንጋ ከተማ በአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች እየተሰራ ያለው ስራ ተስፋ ሰጪ መሆኑን የገለጹት ምክትል ርዕሰ መስተዳሩ ኢንተርፕራይዞችን ለማገዝ የክልሉ መንግሥት ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን እንደሚሰራ ጠቅሰዋል፡፡

የክልሉ ኢንተርፕራይዞችና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ግዛው ጋጊያብ የስራው እንቅስቃሴ ለሌሎች አካባቢዎች ተሞክሮ መሆን የሚችል መሆኑን ጠቅሰው የግብዓትና ብድር አቅርቦት እንዲሁም የገበያ ትስስር ለኢንተርፕራይዞች ለማመቻቸት የክልሉ መንግስት በትኩረት የሚሰራው መሆኑን ተናግራዋል።

ኢንተርፕራይዞችም የግብዓትና ብድር አቅርቦት እንዲሁም የገበያ ትስስር ችግር መኖሩን ገልጸው የክልሉ መንግስት ተገቢውን ድጋፍና እገዛ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።

አጠቃላይ የኢንተርፕራይዞቹ የስራ እንቅስቃሴ በጥሩ ደረጃ ላይ የሚገኝ መሆኑ በጉብኝቱ ተመልክቷል።

ጉብኝታቸውም አፒኔክ አግሮ ኢንዱስትሪ፣ ሀኒት ዳቦና እንጀራ አምራች እና አከፋፋይ ማህበር፣ የኛ እንጨትና ብራታ ብረት ማህበር፣ ምንተስኖት ጌታ እንጨትና ብረት ማህበር እንዲሁም ዳማሲን ቅመማ ቅመም ማቀነባበሪያ ማህበር መሆኑ ተገልጿል፡፡