መጋቢት 27/2015 (ዋልታ) ከመጋቢት 15 እስከ 21 ቀን 2015 ዓ.ም በተደረገው ክትትል ከ163 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መያዙን የጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
ኮሚሽኑ 109 ነጥብ 8 ሚሊየን የገቢ እና 52 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የወጪ ዕቃዎች በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች መያዛቸውን ነው ያስታወቀው፡፡
የገቢ ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር ረገድ አዋሽ፣ ሞያሌ እና ድሬዳዋ ቅርንጫፎች ቀዳሚውን ስፍራ እንደሚይዙ የገለጸው ኮሚሽኑ በቅደም ተከተላቸውም 41 ሚሊየን፣ 15 ነጥብ 6 ሚሊየን እና 15 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን መያዛቸውን ባወጣው መረጃ አመልክቷል፡፡
ከተያዙት ዕቃዎች መካከል አልባሳት፣ ነዳጅ፣ የቁም እንስሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ መድኃኒት፣ ተሽከርካሪዎች፣ የመዋቢያ ዕቃዎች የጦር መሳሪያዎች፣ ጫት፣ አደንዛዥ እጾች፣ የምግብ ዘይት እና የተለያዩ ሀገር ገንዘቦች ይገኙበታልም ነው የተባለው፡፡