ጉዳይ ለማስፈፀም ቢጫ ትኬት ቁረጡ በማለት ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ 9 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

መጋቢት 27/2015 (ዋልታ) ጉዳይ ለማስፈፀም ቢጫ ትኬት ቁረጡ በማለት በተለያዩ አካባቢዎች በተሽከርካሪ እየተንቀሳቀሱ የማታለል ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ 9 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ።

ተጠርጣሪዎቹ ወንጀሉን የሚፈፅሙት የኢሚግሬሽን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲሁም የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጉምሩክ ሰራተኛ እና የስራ ኃላፊ በመምሰል መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ባወጣው መረጃ አመላክቷል፡፡

በተጠቀሱት ተቋማት ለጉዳይ የሚመጡት ተገልጋዮች የያዙትን ሞባይል ስልክ፣ ገንዘብ፣ ቦርሳ እንዲሁም ያደረጉትን ጌጣጌጥ በትኩረት ከተመለከቱ በኋላ ተጠርጣዎቹ በመረጡት ሰው ላይ ወንጀሉን እንደሚፈፅሙም ተመላክቷል፡፡

በዚህም ”ወደ ተቋሙ ውስጥ ለመግባት ቢጫ ትኬት ያስፈልጋል፤ ትኬቱ ከሌላችሁ ወደ ውስጥ መግባት ስለማይቻል በ55 ብር ቆርጣችሁ ኑ፤ ልትቆርጡ ስትገቡ ግን ምንም አይነት ገንዘብም ሆነ ንብረት ይዞ መግባት ስለማይቻል እዚህ አስቀምጣችሁ ሂዱ“ የሚል የማታለያ ዘዴ በመጠቀም ለወንጀል ተግባር በሚንቀሳቀሱበት ተሽከርካሪ ውስጥ ንብረቱ እንዲቀመጥ ካደረጉ በኋላ  የግል ተበዳይ የተነገራቸውን አምነው ትኬት ለመቁረጥ ወደ ውስጥ ሲገቡ ተጠርጣዎቹ ንብረቱን ይዘው እንደሚሰወሩ በምርመራ ተረጋግጧል፡፡

ፖሊስ እንዲህ አይነቱን ወንጀል ለመከላከል እና የፈፃሚዎቹን ማንነት አውቆ ለመያዝ በተለይም ወንጀሉ ይፈፀምባቸዋል በተባሉ አካባቢዎች ላይ የተጠናከረ ጥበቃ እና ክትትል ሲያደርግ መቆየቱን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅሷል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ለወንጀሉ ተግባር ሲጠቀሙባቸው የነበሩ የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3-A 75522 አ.አ እና የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3-B 08277 አ.አ ተሽከርካሪዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል የምርመራ ስራው መቀጠሉንም ገልጿል፡፡