ዱባይ ኢንቨስትመንት ፓርክ በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ፓርክ ለመገንባት ፍላጎት እንዳለው ገለጸ

መጋቢት 27/2015 (ዋልታ) ዱባይ ኢንቨስትመንት ፓርክ በኢትዮጵያ ግዙፍ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለመገንባት ፍላጎት እንዳለው ገለጸ፡፡

በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ የተመራ ልዑክ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የሚገኘውን ዱባይ ኢንቨስትመንት ፓርክ ጎብኝቷል።

ልዑኩ ከጉብኝቱ ባሻገር ከፓርኩ ኢንተርናሽናል ኮሜርሻል ማናጀር ሳሊም አል ሀጀሪ ጋር በኢንቨትመንት ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይቷል።

የዱባይ ኢንቨስትመንት ማኔጀር ሳሊም ተቋማቸው ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር በጋራ በመሆን በኢትዮጵያ በ1 ሺሕ ሄክታር መሬት ላይ ያረፈና የማምረቻ ስፍራዎችን፣ የመኖሪያ አፓርትመንቶችን እንዲሁም የአስተዳደር ህንፃዎችን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ስፍራዎችን ያካተተ ግዙፍ ኢንዱስትሪ ፓርክ መገንባት እና ማስተዳደር እንደሚፈልግ ገልጸዋል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ከዚህ ቀደም ከዱባይ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ጋር በበይነ መረብ ግንኙነቶችን ሲያደርግ የቆየ ሲሆን የነበረውን ግንኙነት በማሳደግና ዝርዝር ጉዳዮች ላይ በጋራ በመስራት ወደ ኢንቨስትመንት ትግበራ ለመግባት ያለመ ውይይት ነው የተደረገው።

የዱባይ ኢንቨስትመንት ፓርክ ዱባይ ላይ ከሚገኙ ትልልቅ ኢንቨስትመንቶች አንዱ ሲሆን 2300 ሄክታር ላይ ያረፈ እና ከ8 ሺሕ በላይ ሰራተኞችን የሚያንቀሳቅስ ግዙፍ ፓርክ መሆኑን የኮርፖሬሽኑ መረጃ አመላክቷል።