የልዩ ኃይል ሪፎርም የሚካሄደው የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት የሚያረጋግጥ የጸጥታ ኃይል ለመገንባት ነው- የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ

ግርማ የሽጥላ

ሚያዝያ 3/2015 (ዋልታ) የልዩ ኀይል ሪፎርም የሚካሄደው የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት የሚያረጋግጥ፣ የሀገርን አንድነት የሚያጸና ጠንካራ የጸጥታ ኃይል ለመገንባት ነው ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባልና የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ግርማ የሽጥላ አስታወቁ፡፡

የአማራ ልዩ ኃይል መከላከያ ሠራዊት በተከዳበትና ሀገር ኅልውናዋ አደጋ ውስጥ በገባበት ወቅት መስዋእትነት የከፈለ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ኃላፊው ከአሚኮ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት የልዩ ኃይል ሪፎርም የሚካሄደውም የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት የሚያረጋግጥ፣ የሀገርን አንድነት የሚያጸና ጠንካራ የጸጥታ ኃይል ለመገንባት ነው።

የልዩ ኃይል ሪፎርምን ተከትሎ በአማራ ክልል የተፈጠሩ አለመግባባቶች ምክንያታቸው ጉዳዩን በሚመለከት የግንዛቤ ሥራ በአግባቡ ባለመሠራቱ ነው ብለዋል።

የክልል ልዩ ኃይሎችን ሪፎርም የማድረጉ ጉዳይ የቆየ ውሳኔ ነው ያሉት ኃላፊው በሰሜኑ ግጭት ምክንያት ተግባሩ መዘግየቱን አብራርተዋል።

በክልሉ መከላከያ ሠራዊት ሲንቀሳቀስ ሌላ ኃይል እንደገባ ተደርጎ የሚሠራጨው አጀንዳ አንድ ጠንካራና ወጥ መከላከያ ለመገንባት የሚደረገውን ሂደት የሚጎዳ እንደሆነም ገልጸዋል። ወደ አማራ ክልል ምንም አይነት የተለየ ኃይል እንዳልገባም አረጋግጠዋል።

የአማራ ሕዝብ የደረሰበትን መፈናቀል፣ ሞት እና አለመረጋጋት የክልሉ መንግሥትና ብልጽግና ፓርቲ በልዩ ትኩረት ችግሩን ለመፍታት እየሠሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

በተለይም ከክልሉ መሪዎች እውቅና ውጭ ከልዩ ኃይል ሪፎርም ጋር በተያያዘ በማኅበራዊ ሚዲያ ልዩ ኃይሉ ትጥቅ እንደሚፈታ ተደርጎ የተሠራጨው መረጃ ትክክል አለመሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

በሪፎረሙ ትጥቅ ስለመፍታት የተላለፈ ውሳኔ እንደሌለም አረጋግጠዋል። በቀጣይም በሰከነ መንገድ በጉዳዩ ላይ በመወያየት የመልሶ ማደራጀት ተግባሩ እንደሚከናወን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ እንደሀገር አስተማማኝ ሰላም ያስፈልጋታል ያሉት የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ግርማ የሽጥላይህንን ለማሳካትም የአማራ ክልል በትልቅ ኀላፊነት እየሠራ ነው ብለዋል።

የአማራ ልዩ ኃይል በክልሉ ሕዝብና መንግሥት ትልቅ ዋጋ ተከፍሎበታል ይህ ኃይልም ፖለቲካዊ ትርጉሙ ከፍ ያለ ነው ብለዋል። ይልቁንስ የሀገርና የሕዝብ አለኝታነቱን ይበልጥ የሚያሳይበትን አደረጃጀት ተከትሎ እንዲደራጅ ይደረጋል ነው ያሉት።

የአማራ ክልል በጦርነት ውስጥ የቆየ ነው፤ የመልሶ ማቋቋም ሥራዎች እየተከናወኑ በመሆኑ እነዚህ ተስፋ ሰጭ ሥራዎችም መሰናከል የለባቸውም ብለዋል።

መንግሥት ሁሉንም ነገር በውይይት ለመፍታት ዝግጁ መሆኑን ያስታወቁት ኃላፊው በዚህ ወቅት በመደማመጥ ችግሮችን በመፍታት ለአማራ ሕዝብ የሚያስፈልገው ሰላም መሆኑን አስገንዝበዋል።