ግብፅ በድብቅ ሮኬቶችን ለሩሲያ ለማቅረብ ማቀዷ ተሰማ

ሚያዝያ 3/2015 (ዋልታ) ግብፅ በድብቅ ሮኬቶችን ለሩሲያ ለማቅረብ ማቀዷን ሾልኮ የወጣ ሰነድ አመላከተ፡፡

የግብፅ ፕሬዝዳንት አብደልፋታህ ኤል ሲሲ ለሩሲያ የሚቀርቡ 40 ሺሕ ሮኬቶችን ለማዘጋጀት አቅደው የሀገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት እና የጦር መሪዎች በሚስጥር እንዲይዙ አሳስበው እንደነበር ነው ሰነዱ የጠቆመው፡፡

ድርጊቱም ከምዕራባዊያን የሚመጣባቸውን ችግር ለማስወገድ ያለመ እንደነበር ዋሽንግተን ፖስት አገኘሁት ያለውን ሰነድ ዋቢ አድርጎ ዘግቧል፡፡

ሚስጥራዊ ሰነዱ ከቅርብ ወራት ወዲህ በተለያዩ ማህበራዊ ድረ-ገጾች ላይ ሾልከው ከወጡ ሰነዶች መካከል መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የአሜሪካ መንግስት ባለስልጣን በእቅዱ ዙሪያ ምንም አይነት መረጃ የለንም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ሰነዱ እውነት ከሆነ ግብፅ ከሞስኮ ጋር ጠንካራ ግንኙነት መመስረት የምትችል ቢሆንም ከአሜሪካ ጋር የሚኖራት የወደፊት ግንኙነት ግን ምን ሊመስል እንደሚችል መገመት ከባድ ይሆናል፡፡