አልሸባብ ሊፈፅም የሞከረው የጥፋት ሴራ በመከላከያ ሠራዊቱ ጥንካሬ ሙሉ በሙሉ መክሸፉን የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት አስታወቀ

ሰኔ 1/2015 (ዋልታ) አልሸባብ ሊፈፅም የሞከረው የጥፋት ሴራ በመከላከያ ሠራዊቱ ጥንካሬ ሙሉ በሙሉ መክሸፉን የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት አስታወቀ፡፡

አልሸባብ በተለያዩ ጊዜያት በምስራቁ የሀገራችን ክፍል ስጋት ለመፍጠር የጥፋት ሙከራዎችን ቢያደርግም በጀግኖች ኢትዮጵያውያን ሴራው እየከሸፈ የሽብር ቡድኑም መደምሰሱ የሚታወቅ ነው።

ከሰሞኑም አልሸባብ በኢትዮጵያ ሶማሊያ ድንበር ዶሎ ካምባስ በተባለ ቦታ በሁለት መኪና ማለትም በአንድ አይሱዙ እና በአንድ ኮብራ መኪና ሙሉ ፀረ ሰውና ፀረ ተሽከርካሪ ፈንጂዎችን ጭኖ በሠራዊታችን ላይ ጉዳት ለማድረስ ቢሞክርም በጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችን ሁለት መኪናዎች እና ስድስት አሸባሪዎች ከነፈንጂዎቻቸው ዶግ አመድ መሆናቸውን ኮሎኔል ፈይሳ አየለ ተናግረዋል።

አልሸባብ በሁለት መኪና ሙሉ ፈንጂ ጭኖ በሠራዊታችን ላይ ጉዳት ለማድረስ በማሰብ ኬላን በጥሶ ለማለፍ ቢሞክርም በጥበቃ ቦታ ላይ የነበሩት ጀግኖች የመከላከያ ሠራዊት አባላት የጠላት መኪና መሆኑን ቀድመው በመረዳት አባላቱ በታጠቁት መሳሪያ አውድመውታል።

በመሆኑም አልሸባብ ድል እቀዳጅበታለሁ ብሎ ያሴረው ሴራ በጀግኖች የመከላከያ ሠራዊት አባላት ከሽፎበታል።

የክፍለ ጦሩ ህብረት ዘመቻ ኃላፊ ሻለቃ መሃመድ ሮብሌ በቦታው ላይ በመገኘት አልሸባብ በሠራዊታችን ላይ የተለያዩ ትንኮሳዎችን ለመፈፀም ቢሞክርም ቀደምትነትን በመውሰድ የአልሸባብን ሴራ እና ተንኮል እያከሸፉ እንደሚገኙ ገልፀው፤ ምንጊዜም የጥንቃቄ ስልቶችን በመከተል ከአካባቢው የፀጥታ ሃይል እና ከስቪል ህብረተሠቡ ጋር ተቀናጅተን በመሥራታችን ውጤታማ ሆነናል ብለዋል።

ሻለቃ መሃመድ ሁለቱ ጓዶች ማለትም ፶/አ ብሩክ ደበበ እና መሰረታዊ ወታደር ጀማል ሰይድ የአልሸባብን ሴራ በማክሸፍ የሰሩት ጀብድ ኢትዮጵያዊነት ጀግንነት መሆኑን ያረጋገጠ ነው ሲሉ መግለጻቸውን ከኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።