ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ 2ኛውን ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር አስጀመሩ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

ሰኔ 1/2015 (ዋልታ) የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሀገር አቀፍ ሁለተኛውን ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በአፋር ክልል አስጀመሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር ላለፉት አራት ዓመታት በተከናወነው የመጀመሪያው ምዕራፍ አረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር 20 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ወደ 25 ቢሊየን ችግኝ በመትከል በስኬት መጠናቀቁን ገልጸዋል።

ዛሬ የተጀመረው ሁለተኛው ምዕራፍ አረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ለቀጣዮቹ አራት ዓመታት የሚቀጥል እንደሆነ ገልጸው በዚህም ተጨማሪ 25 ቢሊየን ችግኝ ለመትከል መታቀዱን ይፋ አድርገዋል።

እንደ ሀገር ይህንን ማሳካት ከቻልን በዓለም አቀፍ ደረጃ በ8 ዓመታት 50 ቢሊየን ችግኝ በመትከል ቀዳሚ ታሪክ መስራት ያስችለናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለእቅዱ መሳካት ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንዲረባረብ ጥሪ አቅርበዋል።

ከዚህ ውስጥ 60 በመቶ የሚሆኑት ጥምር ደን ግብርና ችግኞች ሲሆኑ 35 በመቶ የሚሆኑት የደን ዛፎች እንዲሁም የተቀሩት 5 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ የውበት ዛፎች መሆናቸውንም ተናግረዋል።

በመርኃ ግብሩ ላይ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ደረሰ አማረ (ከአፋር)